
አዲስ አበባ፡ መስከረም 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ2024 በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን ከቡሩንዲ ብሔራዊ ቡድን ጋር ያደርጋል።
የሁለቱ ሀገራት እግር ኳስ ፌደሬሽኖች ቀድመው በደረሱት ስምምነት መሠረት ሁለቱም የደርሶ መልስ ጨዋታዎች በአዲስ አበባ አበበ ቢቄላ ስታዲየም ይካሄዳሉ፡፡ የመጀመሪያው ጨዋታም ነገ መስከረም 11/2015 ዓ.ም ይካሄዳል።
ሉሲዎቹ ከቡሩንዲ አቻቸው ጋር ላለባቸው የማጣሪያ ጨዋታ ላለፉት 12 ቀናት በአዲስ አበባ ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል ተብሏል፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለ ገብርኤል ለጨዋታው አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልፀዋል።
የአየር ንብረት አለመመቸት እና የሜዳ እጥረት ዝግጅታቸውን በፈለጉት ልክ እዳይሰሩ እንቅፋት ኾኖባቸው እንደነበር ጠቁመዋል።
ተጫዋቾቹ በአካልም በሥነ-ልቦናም ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት አሰልጣኙ ሞሮኮው ለምታስተናግደው የ2024 የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ለማለፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የመልሱ ጨዋታ የፊታችን ማክሰኞ መስከረም 15/2015 ዓ.ም በተመሳሳይ በአበበ ቢቄላ ስታዲየም ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል።
ይኽ በእንዲህ እንዳለ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለ ገብርኤል በብሔራዊ ቡድኑ የሚያቆያቸውን የሁለት ዓመት ውል ለማራዘም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- ባዘዘው መኮንን -ከአዲስ አበባ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!