
ባሕር ዳር፡- ጥር 15/2012ዓ.ም (አብመድ) ወጣቱ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ከፍታ የማድረስ አደራውን እንዲወጣ የጋሞ አባቶች አሳስበዋል።
የዘመናችን ጀግኖችን ለማብሰር እና ለሌላ ጀብድ እንዲነሳሱ ለማድረግ ያለመ መርሀ ግብር ትናንት ምሽት በባሕር ዳር ተካሂዷል፡፡ በዝግጅቱ የጋሞ አባቶች፣ የከተማ አሥተዳድሩ የሥራ ኃላፊዎችና ወጣቶች ታድመዋል፡፡ አባቶቹም ወጣቱ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ከፍታ የማድረስ አደራውን እንዲወጣ አሳስበዋል። በአባቶች ታሪክ ከመመካት ባለፈ የእራሱን ታሪክ በመሥራት ለቀጣዩ ትልድ አርዓያ መሆን እንዳለበትም ነው የጠየቁት፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳድር ከንቲባ መሐሪ ታደሰ (ዶክተር) ደግሞ ወጣቱ ትውልድ በሀገራዊ አንድነት ግንባታ ላይ የአባቶቻችን ጀግንነት ሊደግም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ጀግንነት በጦር ሜዳ ብቻ የሚገለጽ ባለመሆኑ በኪነጥበቡ፣ በህክምናው፣ በባሕል ዕድገቱ… በአጠቃላይ በየተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ሁሉ ውጤታማ ሥራ በመሥራት ጀግና መሆን እንደሚገባም ዶክተር መሐሪ አስገንዝበዋል። ለሀገር መልካም ነገር እየሠሩ ለሚገኙት የጋሞ አባቶችም የሰላም እና የፍቅር ጀግኖች በመሆናቸው ምስጋና ቀርቦላቸዋል። ወጣቱ ከጋሞ አባቶች ሰላምን፣ ፍቅርን እና ይቅርባይነትን ተምሮ ለሀገር አንድነት መሥራት እንደሚገባውም የመርሀ ግብሩ ታዳሚያን ጠይቀዋል፡፡
የደግ ኢትዮጵያውያን የስልጠና ማዕከል መሥራች እና የፕሮግራሙ አዘጋጅ አቶ ቤንጃሚን ወንዴ የአብዛኛዎቹ ሀገራት የኃያልነታቸው እና የዕድገታቸው ምስጢር አስተሳሰብ ላይ ተኩረት ሰጥተው መሥራታቸው እንደሆነ አስገንዝበዋል። አስተሳሰብ ላይ መሥራት ሀገር ላይ መሥራት ነውና ተቋማትም የሰው አዕምሮ ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ ነው በመርሀ ግብሩ ተሳታፊዎች የተነሳው፡፡
“የተሠራ አዕምሮ የፈረሰን ከተማ ይሠራል፤ ያልተሠራ አዕምሮ የተሠራ ከተማን ያፈርሳል!” በሚል መሪ ሀሳብ የተካሄደውን መርሀ ግብር የደግ ኢትዮጵያውያን የስልጠና ማዕከል ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳድር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር ነው ያዘጋጁት፡፡
ዘጋቢ፡-ዳግማዊ ተሠራ