
ባሕር ዳር: መስከረም 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በላቲቪያ ሪጋ በሚካሄዱ የጎዳና ላይ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የማሸነፍ ቅድመ ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡
በጎዳና ውድድሩ አምስት የዓለም ሪከርድ የሰበሩ አትሌቶች ይሳተፉበታል። የኦሎምፒክ እና የዓለም ሻምፒዮን አትሌቶችን ጨምሮ 347 አትሌቶች በስድስት ርቀቶች ይሳተፋሉ፡፡
ኢትዮጵያ ከመስከረም 20 እስከ 21 ቀን 2016 ዓ.ም በሚካሄደው ውድድር በሦስት ርቀቶች በ19 አትሌቶች ትወከልላለች።
በሪጋ የአንድ ማይል የጎዳና ውድድር ኢትዮጵያውያኖቹ ድርቤ ወልተጂ እና ፍሬወይኒ ሃይሉ በውድድሩ የማሸነፍ ቅደመ ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡
በዚሁ ርቀት የ5 ሺህ ሜትር ባለ ክብረ ወሰኗ ኬንያዊቷ ፌዝ ኪፕዮገን እና አውስተራሊያዊቷ አትሌት ጄሲካ ሃል ከባድ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡
በ5 ኪሎ ሜትር በሚደረገው ውድድር በሴቶች አትሌት መዲና ኢሳ፣ ለምለም ሃይሉ እና እጅጋየሁ ታዬ ሲሳተፋ÷ በወንዶች በሪሁ አረጋዊ ፣ ዮሚፍ ቀጄልቻ እና ሀጎስ ገብረ ሕይወት ኢትዮጵያን ይወክላሉ።
በሌላ በኩል በወንዶች ግማሽ ማራቶን ጀማል ይመር ፣ ንብረት መላክ ፣ ድንቃለም አየለና ፀጋዬ ኪዳኑ ኢትዮጵያን ሲወክሉ÷ በሴቶች ደግሞ መስታወት ፍቅር፣ ፅጌ ገብረሰላማ፣ ያለምጌጥ ያረጋል እና ፍታው ዘራይ እንደሚሳተፉ ኤፍ ቢ ሲ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!