በሥነ-ምግባር ግድፈት መንግሥት ሊያጣው የነበረ ከ268 ሚሊየን ብር በላይ ማዳን ችለናል” የጉምሩክ ኮሚሽን

38

ባሕር ዳር: መስከረም 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሥነ-ምግባር ግድፈትና በአሰራር ጥሰት መንግሥት ሊያጣው የነበረ ከ268 ሚሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉን የጉምሩክ ኮሚሽን ገለጸ፡፡

በኮሚሽኑ የኦፕሬሽን ዘርፍ ም/ኮሚሽነር አዘዘው ጫኔ÷ በኮሚሽኑ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች እንቅፋት እንዳይገጥማቸውና ሌብነትና ብልሹ አሠራርን ከምንጩ ለማድረቅ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ የሥነ-ምግባር መከታተያ ሥርዓት ሥራውን ሳይንሳዊ ወደሆነ የተቋማዊ ስጋትና ሥራ አመራር ሥርዓት ማሸጋገሩን አንስተዋል፡፡

በ2016 በጀት ዓመትም የተቋሙን ጤንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል ነው ያሉት፡፡

የተቋማዊ ስጋት ሥራ አመራርና ሥነ-ምግባር ዳይሬክተር ሰርካለም አበበ ኮሚሽኑ ተልእኮውን በአግባቡ እንዳይወጣ ሌብነትና ብልሹ ሥነ-ምግባር ቀዳሚ ተግዳሮቶች መኾናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ባለፈው በጀት ዓመት በሥነ-ምግባር ግድፈትና በአሠራር ጥሰት መንግሥት ሊያጣው የነበረ 268 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ማዳን መቻሉን አስታውሰዋል።

በበጀት ዓመቱ በተለያዩ የሥነ-ምግባር ጥሰቶች 417 አመራሮችና ሰራተኞች ላይ የዲሲፕሊንና አሥተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በባሕርዳር ከተማ ከ71 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመከታተል ተመዝግበዋል” የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ
Next articleበሪጋ 2023 የጎዳና ላይ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይጠበቃሉ።