
ባሕር ዳር: መስከረም 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል የተማሪዎች ምዝገባ ከነሐሴ 23/2015 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ነው፡፡
በክልሉ በተፈጠረው ወቅታዊ የሰላም እጦት እስከ ጳጉሜን 3/2015 ዓ.ም ድረስ የነበረው የተማሪዎች ምዝገባ እስከ መስከረም 11 መራዘሙ ይታወሳል፡፡
በክልሉ የተማሪዎች ምዝገባ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት የተማሪዎች ምዝገባ ተቀዛቅዟል፡፡
የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ የዕቅድና መረጃ ቡድን መሪ ይፍቱሥራ ዋሴ በከተማ አሥተዳደሩ በ2016 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡ በከተማ አሥተዳደሩ ለ2016 የትምህርት ዘመን 143 ሺህ ተማሪዎችን ለመመዝገብ አቅደው እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ ዛሬ መስከረም 10/2016 ዓ.ም የተመዘገቡ ተማሪዎችን ሳይጨምር 71 ሺህ 752 ተማሪዎችን መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡
በከተማ አሥተዳደሩ ባለፉት ዓመታት የሚመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር መቀነስ እንደማይገጥም ያስታወሱት ቡድን መሪዋ ዘንድሮ በክልሉ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት የተማሪዎች ምዝገባ መቀዛቀዙን ነው የተናገሩት፡፡ በከተማ አሥተዳደሩ ይመዘገባሉ ተብሎ የሚጠበቁ ተማሪዎችን ለማስመዝገብ ርእሳነ መምህራንና ሱፐር ቫይዘሮች ከማኅበረሰቡ ጋር እየተወያዩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ እያደረጉ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ወላጆች ከትምህርት ክፍያ ጋር በተያያዘ ሲያነሱት የነበረውን ቅሬታ መፍታታቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ከተማዋ ሰላም በመኾኗ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ልከው ማስመዝገብ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡
የስምንተኛ ክፍል ውጤታቸውን ያወቁ ተማሪዎች ምዝገባ መጀመራቸውንም ገልጸዋል፡፡ ምንም ችግር ቢፈጠር ትምህርት መቅረት የሌለበት ጉዳይ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ የተማሪዎችን የምዝገባ ሂደት እየተከታተሉ ተማሪዎች እንዲመዘገቡ እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ከወላጆች እና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መጥተው እንዲመዘገቡ ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!