“ሁላችንም ለችግረኛ ቤተሰብ ልጆች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ የበጎነት አሻራችንን ማሳረፍ አለብን ” የአማራ ክልል ሴቶች ፣ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ

60

ባሕር ዳር: መስከረም 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የነገ የሀገር ተስፋዎች ዛሬን በልኩ ተምረው ለቁምነገር እንዲበቁ፣ የሀገር አለኝታነታቸውም እውን እንዲኾን በቅንጅት ተባብሮ መሥራትን ይጠይቃል፡፡

እናም ልጆች ላይ መሥራት ሀገር ላይ መሥራት ነውና ከሰብእና ግንባታ እስከ በዕውቀትና ክህሎት አንጾ ማሳደግ ከወላጆች ፣ ከማኅበረሰቡ ፣ ከትምህርት ቤቱ ፣ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ፣በጥቅልም ከመንግሥት የጋራ ርብርብ ማድረግ ተገቢ ይኾናል፡፡

በተለይም የችግረኛ ቤተሰብ ልጆች በወላጆች ወይም አሳዳጊዎቻቸው የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት የዛሬ ተማሪዎች ከነገ የሀገር ሕልማቸውና ሚናቸው እንዳይናጠቡ የቅን ልቦች ድጋፍ እጅጉን ያስፈልጋል፡፡

የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ምጥን ብርሐኑ እንደሚሉት የአዲስ ዓመት መምጣትን ፣ በአዲስ የትምህርት ዘመን መጀመርን ምክንያት በማድረግ ለችግረኛ ቤተሰብ ልጆች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ እየተለመደ የመጣ መልካም እሴት ኾኗል፡፡

ቢሮው ድጋፍ ለሚሹ የችግረኛ ቤተሰብ ተማሪዎች ለጋሾችን ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እያስተባበረ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያገኙ እየሠራ ስለመኾኑም ነው የተናገሩት፡፡

ተቋሙ በቅንጅትም በተናጠልም ወደ ትምህርት ቤት የሚያቀኑ ልጆች ሁሉ ሙሉ የትምህርት ቁሳቁስ እንዲሟላላቸው አልሞ በመሥራት ላይ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ፣ግለሰቦችና ከበጎ አድራጊ ድርጅቶች በተሰበሰበ ገንዘብ ለችግረኛ ቤተሰብ ልጆች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ እየተደረገ መኾኑንም አስረድተዋል፡፡

በክልሉ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ባለባቸው አካባቢዎች ሁሉ ድጋፉ እየተከናወነ መኾኑን የተናገሩት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊዋ በአብነት ከጠቀሷቸው ቦታዎችም ባሕር ዳር ከተማ ፣ ደሴ ከተማ ፣ ደቡብ ወሎ ዞን ፣ ሰሜን ወሎ ዞን እና ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞንን ጠቅሰዋል፡፡

እስከ አሁን ባለው መረጃም፡-
👉ደሴ 6 ሺህ ደርዘን ደብተር እና እስክርቢቶ

👉ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን 258 ደርዘን ደብተር ፣11 ፓኮ ስክርቢቶ ፣ ለአምስት ተማሪዎች የትምህርት ቤት ዩኒፎርም

👉ደቡብ ወሎ ዞን 10 ሺህ 891 ደርዘን ደብተር ፣ 1ሺህ ፓኮ ስክርቢቶ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚኖሩ እና ለችግረኛ ቤተሰብ ተማሪዎች ድጋፍ ተደርጓል ነው ያሉት።

👉ባሕር ዳር ከተማም ሴቶችና ሕጻናት ቢሮን ጨምሮ ሌሎች አካላትም ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

👉ሰሜን ወሎ ዞን 3ሺህ 436 ደርዘን ደብተር ፣ 493 ፓኮ ስክርቢቶ ፣ ለ783 ተማሪዎች ዩኒፎርም በድምሩ ከ5 ሺህ በላይ ተማሪዎች የድጋፉ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ ድጋፉ አዲስ አበባ ከሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ፣ከአካባቢው ማኅበረሰብና ከሌሎችም ለጋሾች እንደተገኘ ጠቅሰዋል፡፡

ኀላፊዋ እንዳሉት ተቋሙ ልጆች ላይ በበጎ ፍቃድ ድጋፍ ለሚያደርጉ አካላት ምሥጋና እና ዕውቅናም እየሰጠ ነው ብለዋል፡፡

ማንኛውም ሰው ለቤተሰቡ የትምህርት ቁሳቁስ ሲገዛ የችግረኛ ቤተሰብ ልጆችን ማሰብ አለበት ፤ ከጎረቤቱ ጀምሮ የሚችለውን ድጋፍ ማድረግን ማሰብ አለበት መልእክታቸው ነው፡፡

“ሁላችንም ለችግረኛ ቤተሰብ ልጆች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ የበጎነት አሻራችንን ማሳረፍ አለብን” ነው ያሉት፡፡ ሀገር የሚገነባው፣ ትውልድ የሚቀረጻው በትብብር ፣በመደጋገፍና በመተሳሰብ በጎ ተግባር ነው የሚሉት ወይዘሮ ምጥን መልካም እሴቶችን ማጎልበት እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡

ሀገር ወዳድ ትውልድ ለመገንባት ፣መልካም ዜጋም ለመፍጠር ፣ለልጆች አርዓያነትን ማሳየት፣አለኝታነትንም ማረጋገጥ ይገባል ነው ሚሉት ወይዘሮ ምጥን፡፡

እናም ሁላችንም ካለን በማካፈል ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ተማሪዎችን ሁሉ የተሟላ የትምህርት ቁሳቁስ እንዲኖራቸው ድጋፋችን አጠናክረን እንቀጥል ጥሪያቸው ነው፡፡

ዘጋቢ፡- ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ቱሪዝም በባህሪው ሰላም እና ምቹ ከባቢን ይፈልጋል” ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ
Next article“በባሕርዳር ከተማ ከ71 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመከታተል ተመዝግበዋል” የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ