“ቱሪዝም በባህሪው ሰላም እና ምቹ ከባቢን ይፈልጋል” ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ

87

ባሕር ዳር: መስከረም 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊ እና ባሕላዊ መስህቦችን ከታደሉ የኢትዮጵያ አካባቢዎች አንዱ አማራ ክልል ነው፡፡ ክልሉ ከራስ ደጀን እስከ ላሊበላ፣ ከግሸን እስከ አቡነ ዮሴፍ፣ ከጮቄ እስከ ጉና፣ ከመንዝ ጓሳ ምድር እስከ ጎንደር አብያተ መንግሥታት ጎብኝዎችን የሚያለምዱ እና ከተፈጥሮ ጋር የሚያዛምዱ መስህቦች አሉት፡፡

ምንም እንኳን የዓለም ጎብኝዎችን ቀልብ የሚስቡ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች በክልሉ ቢኖሩም ያለፉት አራት እና አምስት ዓመታት ግን ለቱሪዝም ዘርፉ ምቹ የሚባሉ አልነበሩም፡፡ ዓለም አቀፋዊ ወረርሽኝ የነበረው የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ተከትሎ እንቅስቃሴው ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የተገታው ቱሪዝም እንደ ኢትዮጵያ ነባራዊ ኹኔታ ደግሞ ከዚያም የተሻገረ ፈተና ተደቅኖበት ቆይቷል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት ዓመታት የተስተዋለው ደም አፋሳሽ ጦርነት ለቱሪስት መስህብነት የተፈጠሩትን የተራራ ሰንሰለቶች የጦርነት አውድማ አድርጓቸው ቆይቷል፡፡ ችግሩ በቱሪዝም የሚገኘውን ሃብት ከማሳጣቱም በላይ የመስህብ ቦታዎችን የደህንነት ስጋት ውስጥ ከትቷቸው ቆይቷል፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አንጻራዊ ሰላም ከታየበት በኋላም በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ ስጋት በቱሪዝም እንቅስቃሴው ላይ የተስተዋለ ሌላኛው ፈተና ኾኗል ያሉን የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር መልካሙ አዳም ናቸው፡፡

በክልሉ እስከ 250 ሺህ የውጭ ቱሪስቶች የተመዘገቡበት ወቅት ቢኖርም በ2015 ዓ.ም ወደክልሉ የመጡ ጎብኝዎች ቁጥር ከ30 ሺህ አይበልጥም ነው ያሉት፡፡

“ቱሪዝም በባህሪው ሰላም እና ምቹ ከባቢን ይፈልጋል” የሚሉት ዳይሬክተሩ ላለፉት ዓመታት የተስተዋለው ግጭት የቱሪዝም ገቢውን ከመቀነሱም በላይ የክልሉን ሰላማዊ ገጽታ እንዳያበላሸው ጥንቃቄ ይፈልጋል ብለዋል፡፡ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የቱሪስት መስህቦች እንዳይጎዱም የየአካባቢው ማኅበረሰብ ጥበቃ ሊያደርግ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የተጎዳውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ወደነበረበት ለመመለስ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ይጠይቃል ያሉት አቶ መልካሙ በየጊዜው የሚፈጠሩትን ሕዝባዊ፣ ሃይማኖታዊ እና መንግሥታዊ በዓላት በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleመሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅት ከጎዳና ላይ ያነሳቸውን ወጣቶች እና እናቶችን የሕይወት ክህሎት አሠልጥኖ አስመረቀ፡፡
Next article“ሁላችንም ለችግረኛ ቤተሰብ ልጆች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ የበጎነት አሻራችንን ማሳረፍ አለብን ” የአማራ ክልል ሴቶች ፣ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ