መሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅት ከጎዳና ላይ ያነሳቸውን ወጣቶች እና እናቶችን የሕይወት ክህሎት አሠልጥኖ አስመረቀ፡፡

54

ባሕር ዳር: መስከረም 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)መሰረት የበጎ አድራጎት ማኅበር ከአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ውል ወስዶ የጎዳና ላይ ወጣቶችን በማንሳት የሕይወት ክህሎት ሥልጠና በመሥጠት ከወላጆቻቻው የማቀላቀል እና ሴቶችንም ቋሚ ሥራ እንዲፈጥሩ እያደረገ ነው። በዛሬው ዕለትም 80 ወጣቶችን፣ አምስት ሴቶችን እና 36 ሕጻን የያዙ እናቶችን አሠልጥኖ አስመርቋል፡፡

ከተመራቂዎች መካከል ወጣት ሰብለ አሰም ትገኝበታለች፡፡ አካል ጉዳተኛና የጎዳና ተዳዳሪ ናት፡፡ ሰብለ ቤተሰቦቿን አታውቃቸውም፡፡ ሆስፒታል ተወልዳ ሆስፒታል አደገች፡፡ ያሳደጋት ሆስፒታል ዕውቀት እንድትቀስም ቢያደርግም ውጤት ማምጣት አልቻለችም፡፡ የውጤቷ መቅረት እና የነበረባት የአቻ ግፊት ሕይወቷን ለጎዳና ዳረገው፡፡ ጎዳና ላይ እያለች ብዙ መከራ ተቀበለች፡፡ ለሱስ ተጋለጠች። ጎዳና ላይ ለአምስት ዓመት ስቆይ በሱስ ከመጠመድ ውጪ ያተረፍኩት አንዳች ነገር የለም ትላለች ሰብለ፡፡ ከሱስ መላቀቅ ግን ይቻላል ትላለች፡፡

በተሰጣት የሕይወት ክህሎት ሥልጠና ተጠቅማ ዶሮ ለማርባት ተዘጋጅታለች፡፡ ሰብለ እሷ ወዳሳለፈችው አስከፊ ወደኾነው የጎዳና ሕይወት ሌሎችም እንዳይገቡ የእህትነት ምክሯን ለግሳለች፡፡

ሌላው ተመራቂ ወጣት ምስክር አሕመድ ከጋይንት ወረዳ ነው የመጣው፡፡ ለሦስት ዓመታት ጎዳና ተዳዳሪ ኾኖ ቆይቷል፡፡ ከተማ ገብቶ በመሥራት እናቱን ለማገዝ የነበረው ሕልም ሳይሳካለት ቆይቷል፡፡ ጎዳና ላይ አስከፊ ሕይወትን መርቷል፡፡ ሳልሰርቅ ሰርቀሃል ተብዬ ተደብድቤለሁ ፤ የምቀምሰው ምግብ ሳጣ ለምኛለሁ ይላል ምስክር።

ምስክር አሕመድ አሁን ከሱስ ተላቅቋል፡፡ የወሰደው ሥልጠና የወደፊት ሕይወቱን የሚመራበት ሥራ ለመሥራት እና እናቱን ለማገዝ ወኔ የሰነቀበት እንደኾነም ተናግሯል።

የመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ታደለ ኅሩይ ድርጅቱ በሦስቱ ዘርፎች ማለትም በሕጻናት፣ በወጣቶች እና ሕጻን በያዙ እናቶችን ዘርፍ ሥልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ልጆችን ከጎዳና ላይ አንስተው የሕይወት ክሕሎት ሥልጠና እየሰጡ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ድርጅቱ ከመንግሥት በወሰደው ውል መሰረት 196 ሰዎችን በመልሶ ማቋቋም ሥራው እያሳተፈ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ ታዳለ ሠልጣኞቹ ከሥልጠና በተጨማሪ የምግብ፣ መጠለያ እና የጤና አገልግሎት ሲያገኙ መቆየታቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ልጆችን ከወላጆቻቸው የማገናኘት ዝግጅት ስለመጠናቀቁም ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዝና ጌታቸው ቢሮው ከከተማ ሴፍቲኔት ባገኘው ድጋፍ በችግር ውስጥ ያሉ አረጋውያንን፣ ጽኑ ሕሙማንን እና የጎዳና ተዳዳሪዎችን በማንሳት የመደገፍ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

ሥራው በክልሉ አራት ከተሞች ላይ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል፡፡ ደሴ፣ ጎንደር፣ ባሕር ዳር እና ደብረ ብርሃን ከተሞች በሴፍትኔቱ ታቅፈው ሥራ የሚከናወንባቸው ከተሞች ስለመኾኑም አንስተዋል፡፡

ወይዘሮ ዝና በክልሉ ከሚሠሩ 11 ድርጅቶች ውስጥ መሰረት የበጎ አድራጎት ማኅበር አንዱ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ማኅበሩ ጎዳና ላይ የሚወጡ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የኾኑ ወጣቶችን በማንሳት የሕይወት ክሕሎት ሥልጠና እየሰጠ እና ወደ ቤተሠቦቻቻው እየመለሰ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ ኀላፊዋ ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅም በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል ፡፡

በክልሉ 11 ፕሮጀክቶች በመሰል ሥራዎች ላይ እየተሳተፉ መኾኑን የጠቆሙት ምክትል ቢሮ ኀላፊዋ ገንዘብ ብቻ መሥጠት ችግሩን እንደማይቀርፈው ተናግረዋል፡፡ በገንዘብ ከመርዳት ባሻገር ቋሚ ሥራ ኖሯቸው እራሳቸውን የሚያሥተዳድሩበት መንገድ እየተመቻቸ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡

በአማራ ክልል በዚህ ዓመት ከ1 ሺህ 9 መቶ በላይ ወጣቶችን፣ ሕጻናት የያዙ ሴቶችን እና አረጋውያንን ከጎዳና ላይ ለማንሳት መታቀዱንም ምክትል ቢሮ ኀላፊዋ ጠቁመዋል፡፡

በአማራ ክልል በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ከአምስት ሺህ በላይ ወጣቶች የጎዳና ተዳዳሪ መኾናቸውን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ዘጋቢ ፡-ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የደረሰውን የሰሊጥ ሰብል ለመሠብሰብ ከ1 ሚሊዮን በላይ የጉልበት ሠራተኛ ያስፈልጋል” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና መምሪያ
Next article“ቱሪዝም በባህሪው ሰላም እና ምቹ ከባቢን ይፈልጋል” ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ