
ባሕር ዳር፡- ጥር 15/2012ዓ.ም (አብመድ) ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት የክልሉን የቱሪዝም ፍሰት እንደጨመሩት የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡
ቱሪዝም ለአንድ ሃገር ዕድገት እና ለአንድ አካባቢ ሕዝብ ተጠቃሚነት ሚናው የጎላ ነው፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዙ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ መስህብ ቦታዎች ባሉበት እና የሥራ ዕድል ሊፈጠርለት የሚገባ ወጣት በብዛት በሚገኝባቸው ሃገራት ቱሪዝም የተሻለ የሥራ ዕድል አማራጭ ነው፡፡ በመሆኑም ቱሪዝምን የሥራ ዕድል ማድረግ አማራጭ እንደሚሆን እና ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል በመገንዘብ እየተሠራ እንደሆነ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እስታውቋል፡፡
በ2012 ዓ.ም በአማራ ክልል የተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት የክልሉን የቱሪዝም ፍሰት በመጨመር ሚናቸው ከፍተኛ ነበር፡፡ መስከረም መጨረሻ ላይ የግሸን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ ንግስ፣ በታኅሳስ ወር መጨረሻ እንደ ሃገር በተለየ ደግሞ በላል ይበላ ከተማ የተከበረው የልደት በዓል እና ከቀናት በፊት በጎንደር ከተማ የተከበረው የጥምቀት በዓል የክልሉን የቱሪዝም ፍሰት እንዲጨምር አድርገዋል ብሏል ቢሮው፡፡
በአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ኃይለ ኢየሱስ ፍላቴ በዓላቱ የክልሉን ገፅታ ከማስተዋወቃቸው በላይ የቱሪዝም ፍሰቱን አነቃቅተውታል ብለዋል፡፡ ታኅሳስ 28 ቀን 2012 ዓ.ም በላልይበላ ከተማ በተከበረው የልደት በዓል ላይ ብቻ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የሃገር ውስጥ እና የውጭ ሃገራት ጎብኝዎች ተገኝተዋል፡፡ ጥምቀትን በጎንደር ከ2 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንዲታደምበት ለማድረግ ታቅዶ እንደተሠራም አቶ ኃይለኢየሱስ አስታውሰዋል፡፡
በዓላቱ ያለምንም የፀጥታ ችግር መጠናቀቃቸው ደግሞ ለክልሉ የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ፋይዳቸው የጎላ እንደሚሆን ነው የተናገሩት፡፡ “በክልሉ ለቱሪስት መስህብ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ እሴቶች አሉ” ያሉት አቶ ኃይለ ኢየሱስ ዘርፎችን እየለዩ መሥራት የክልሉ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ቱሪዝምን ማስተዋወቅና ማልማት ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚጠይቅ እንደአስፈላጊነቱ እየተለየ ለወጣቶች የሥራ ዕድል በሚፈጥር መልኩ የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ በተለይም ለአብመድ ገልፀዋል፡፡
እንደ ዓለም አቀፉ የቱሪዝም ድርጅት ሪፖርት በ2018 (እ.አ.አ) የቱሪዝም ዘርፉ በአፍሪካ ብቻ በሰባት በመቶ አድጓል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው