“የደረሰውን የሰሊጥ ሰብል ለመሠብሰብ ከ1 ሚሊዮን በላይ የጉልበት ሠራተኛ ያስፈልጋል” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና መምሪያ

103

ሁመራ፡ መስከረም 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በስፋት ከሚመረቱ ምርቶች መካከል ሰሊጥ በዋናነት ተጠቃሽ ነው። የዞኑ ግብርና መምሪያ የደረሰውን የሰሊጥ ሰብል ለመሰብሰብ ከ1 ሚሊዮን በላይ የጉልበት ሠራተኛ እንደሚያስፈልግ አስታውቋል።

በ2015/16 ዓ.ም የምርት ዘመን በዞኑ ከ230 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በሰሊጥ መሸፈኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ አወቀ መብራቱ ገልጸዋል። 1 ሚሊዮን 1 መቶ 52 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል ብለዋል መምሪያ ኅላፊው።

በዞኑ በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥ 41 በመቶ በሰሊጥ ምርት የተሸፈነ ነው ያሉት አቶ አወቀ ፤ አሁን ያለንበት ወቅት ደግሞ የደረሰ የሰሊጥ ሰብል የሚሰበሰብበት ነው ብለዋል፡፡ ከመጪው መስከረም 15/2015 ዓ.ም ጀምሮ የሰሊጥ ሰብል መሰብሰብ ሥራ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

አቶ አወቀ የሰሊጥ ሰብል በወቅቱ ካልተሰበሰበ የምርት ብክነት የሚያስከትል በመሆኑ በዞኑ የደረሰውን የሰሊጥ ሰብል ለመሠብሰብ ከ1 ሚሊዮን በላይ የጉልበት ሠራተኛ ያስፈልጋል ብለዋል። የጉልበት ሠራተኞች ወደ አካባቢው በሚመጡበት ወቅት የትራንስፖርት ችግር እንዳያጋጥማቸው ከአጎራባች ዞኖች ጋር በቅርበት እየተሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የደረሰ ሰብላቸውን ሲንከባከቡ ያገኘናቸው አልሚ ባለሃብት አቶ ብርሃኔ በዓታ በክረምት ወቅት ሰብላቸውን በተደጋጋሚ በማረማቸው እና በመንከባከባቸው ሰብሉ በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝም ነግረውናል። አቶ ብርሃኔ አሁን ላይ የደረሰ ሰብላቸውን ለመሠብሰብ በርካታ የሰው ኀይል እንደሚያስፈልጋቸውም ነግረውናል።

ሌላኛው አልሚ ባለ ሃብት አቶ ገብረመስቀል መንግሥቱ በክረምቱ ወቅት ጸረ አረም እና ጸረ ተባይ ኬሚካሎችን በመጠቀም ማሳቸውን ሲንከባከቡ መቆየታቸውን አንስተው አሁን ላይ የደረሰ ሰብላቸውን ለመሰብሰብ ዝግጅት ላይ መኾናቸውን አጫውተውናል። የደረሰ ሰብልን ለመሰብሰብ የሚመጡ ሠራተኞችን እንደ ቤተሰብ ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጁ መኾናቸውን አንስተዋል።

በአካባቢው ባለው አስተማማኝ ሰላም ሠራተኞች በየትኛውም ቦታ በነጻነት መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ያነሱት አልሚ ባለሃብቶቹ ለሠራተኞች ምቹ መኝታ፣ ከከተማ ወደ እርሻ ቦታ ማጓጓዣ ትራንስፖርት፣ ምግብ፣ በቂ ውኃ እና መድኃኒት ቀድመው ማዘጋጀታቸውንም ነግረውናል።

ዘጋቢ፡- ያየህ ፈንቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአማርኛ ቋንቋ በሩሲያ ሰማይ ሥር”
Next articleመሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅት ከጎዳና ላይ ያነሳቸውን ወጣቶች እና እናቶችን የሕይወት ክህሎት አሠልጥኖ አስመረቀ፡፡