“የአማርኛ ቋንቋ በሩሲያ ሰማይ ሥር”

79

ባሕር ዳር: መስከረም 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የእውነት ዘመዶች የዘመዶቻቸውን ታሪክ ያውቃሉ፣ የክፉ ቀን ወዳጆች የወዳጆቻቸውን ባሕል ይረዳሉ፣ የወዳጆቻቸውን ቋንቋና ማንነት ያውቃሉ፣ የእውነት ዘመዶች ስለ እውነት፣ በእውነት እና የእውነት ይወዳሉ፣ ለዘመናትም በወዳጅነታቸው ይጸናሉ፡፡ የክፉ ቀን ወዳጆች ችግር ሲመጣ ፊታቸውን አያዞሩም፣ በጨነቀ ዘመን አይጠፉም፣ በክፉ በደጉም ዘመን በወዳጅነታቸው ይጸናሉ፣ መከራና ደስታውን በጋራ ይካፈላሉ እንጂ፡፡

የልብ ወዳጅነት ድንበር አይወስነውም፣ ወሰን አይከልለውም፡፡ የሀገሩ ርቀት፣ የመንገዱ ርዝመት፣ የውቅያኖሱ ስፋትና ጥልቀት አያርቀውም፣ የልብ ወዳጅነት ውቅያኖስን እየተሻገረ፣ ዓለሙን እያካለለ ይዳረሳል እንጂ፡፡ ከአውሮፓ ምሥራቅ ንፍቅ፣ ከአፍሪካም ምሥራቅ ንፍቅ በሚገኙ ሁለት የምሥራቅ ሀገራት የኖረ፣ የዳበረ፣ የጠበቀና ዘመናትን የዘለቀ ወዳጅነት አለ፡፡ ከምሥራቅ ብርሃን፣ ከምሥራቅ ፀሐይ፣ ከምሥራቅ ተስፋ ይወጣል እንዲሉ አበው የምሥራቅ እንቁዎች፣ የምሥራቅ ታላቆች ናቸው፡፡ ሁለቱም በዓለም ታሪክ ውስጥ ከፍ ያለ አሻራ አሳርፈዋል፤ የገዘፈ ታሪክ በማይጠፋ ብራና አስፍረዋል ኢትዮጵያና ሩሲያ፡፡

ኢትዮጵያውያን እና ሩሲያውያን ነጻነትን አሳልፈው አይሰጡም፣ በሀገር ክብርና በሠንደቅ ፍቅር አይደራደሩም፣ ለሠንደቅ ፍቅርና ለሀገር ፍቅር ሲዋደቁ ኖረዋል፣ ጠላቶቻቸውን ድል እየመቱ በመሥዋዕትነታቸውም ታላቅ ሀገር አኖረዋል፣ ታላቅ ታሪክ ጽፈዋል፡፡ ኢትዮጵያና ሩሲያ ወዳጅነታቸው ከነገሥታቱ ዘመን ጀምሮ የነበረ፣ በጥብቅ መተማመን ላይ የተሳሳረ እንደኾነ ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያውያን ወደ ሩሲያ፣ ሩሲያውያንም ወደ ኢትዮጵያ እያቀኑ ታሪካቸውን፣ ሃይማኖታቸውን፣ ባሕላቸውን፣ ማንነታቸው እና እሴታቸውን ሲማማሩና ሲተዋወቁ ኖረዋል፡፡ ለዘመናት በቆየው ወዳጅነታቸው ክፉም ደግም ጊዜ አሳልፈዋል፡፡ ዛሬም እንደዚያው፡፡

ሩሲያ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን ለማወቅ ካላት ጽኑ ፍላጎት የተነሳ ኢትዮጵያዊ የኾነውን አማርኛ ቋንቋን ለሕዝቦቿ ስታስተምር ኖራለች፡፡ በአማርኛ ቋንቋ የተጻፉ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችንም አስተርጉማለች፡፡ በዚህ ዘመንም በዋና ከተማዋ በሞስኮ በሚገኙ ትምህርት ቤቶቿ አማርኛ ቋንቋን እየሰጠች ነው፡፡

ጸሐፈ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ አማርኛ ቋንቋ በሩሲያ ሀገር መሠጠት የተጀመረው አሁን አይደለም ይላሉ፡፡ እሳቸው በ1963 ዓ.ም ወደ ቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ወደ አሁኗ ሩሲያ ለትምህርት አቅንተው ነበር፡፡ በዚያም ኖረዋል፡፡ እሳቸው ከመሄዳቸው አስቀድሞም በዚያች ሀገር የአማርኛ ቋንቋ ይሰጥ እንደነበርም ነግረውኛል፡፡ ሩሲያውያን ተማሪዎችም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየመጡ አማርኛ ቋንቋን ይማሩ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በርካታ አማርኛ ተናጋሪ ሩሲያውያን የተፈጠሩት በሀገራቸው በነበሩ የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መኾኑንም ነግረውኛል፡፡

አማርኛ ቋንቋን ተምረው የጨረሱ ሩሲያውያን በኢትዮጵያ ዲፕሎማት ይኾናሉ፡፡ አሁን ላይ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር የኾኑትም አማርኛ ቋንቋን ይናገራሉ፡፡ ከንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ጀምሮ የሞስኮ ራድዮ የሚባል የራድዮ ሥርጭት እንደነበር ያስታወሱት ጋሽ አያልነህ የኢትዮጵያን ባሕልና ታሪክ ለሩሲያውያን፣ የሩሲያን ባሕልና ታሪክ ደግሞ ለኢትዮጵያውያን ሲነገር እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ የራዲዮ ጣቢያው የሩሲያን ሥነ ጽሑፍ ለኢትዮጵያውያን ያስተዋውቅም ነበር፡፡ በራዲዮ ጣቢያው የሚሠሩት አማርኛ ተናጋሪ ሩሲያውያን እንደነበሩም ጋሽ አያልነህ ያስታውሳሉ፡፡

ጋሽ አያልነህ በሞስኮ ራዲዮ ጣቢያ ለሥምንት ዓመታት ሠርተዋል፡፡ “የደራሲው ደብተር” የሚል ዝግጅት ተከፍቶላቸው በሳምንት ሁለት ጊዜ የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍ፣ የሩሲያን ሥነ ጽሑፍ እና የዓለምን ተራማጅ ሥነ ጽሑፍ ያቀርቡበት እንደነበርም ነግረውኛል፡፡ የሩሲያ ዩኒቨርሲቲዎች አማርኛን ዘለግ ላሉ ዓመታት ሲያስተምሩ ቆይተዋል፡፡ ሩሲያውያን የጋሽ አያልነህ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን ጨምሮ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ላይ አሻራ ያሳረፉ ደራሲያንን ሥራዎችም ሲተረጉሙ ኖረዋል፡፡

ሩሲያውያን በራሳቸው ቋንቋ ሳይኾን በራሳችን ቋንቋ ተምረው ነው የቀረቡንም ይላሉ ጋሽ አያልነህ፤ የሩሲያውያንን ጥብቅ ወዳጅነት ሲገልጹ፡፡ ሩሲያውያን ለኢትዮጵያ ትልቅ ክብር የሰጡ ናቸው፣ አማርኛ ቋንቋ ከኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች የሚገባው ያህል ክብር ባልተሰጠበት በአሁኑ ጊዜ ሩሲያን ጨምሮ ሌሎች ሀገራትም አማርኛን እያስተማሩ መኾናቸውን ነው የነገሩኝ፡፡ የአማርኛ ቋንቋን ታላቅነት ብዙ ዓለም እየተቀበለው ነው፣ እንዳለመታደል ኾኖ የአማርኛ ቋንቋ በሀገሩ የሚገባው ክብር አልተሰጠውም፣ ታላቅነቱም በሚገባው ልክ አልታወቀለትም ነው ያሉት፡፡

አማርኛ በቀላሉ የሚሰማ፣ የሚነገር፣ የሚጻፍ እና የሚስፋፋ፣ ጥንታዊ መሠረት ያለው በመኾኑ ታላቅ ክብር እየሰጡት ነው፣ ለሩሲያውያን ልዩ ክብር ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡

ዓለም ፊቱን ባዞረብን፣ ጠላቶች በበረከቱብን፣ በየአቅጣጫው በሚጮሁብን ዘመን ሩሲያውያን ከእኛ ጋር የቆሙ ናቸው ነው ያሉት ጋሽ አያልነህ፡፡ የኢትዮጵያና የሩሲያ ወዳጅነት በሦስት መሠረታዊ መሰሶዎች ላይ የተገነባ ነው የሚሉት ጋሽ አያልነህ ጥንታዊ የንጉሠ ነገሥት ሥርዓት፣ ጥንታዊ የነጻነት አብሪ ኮኮቦች መኾናቸው እና ሃይማኖታዊ ግንኙነታቸው መሠረታዊ መሰሶዎቻቸው መኾናቸውን ነው የነገሩኝ፡፡

በሩሲያ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ስሙ ጎልቶ የሚነሳው ፑሽኪን የዘር ግንዱ ከኢትዮጵያ እንደመጣ የሚያነሳ ታሪካዊ ዳራ ያለው በመኾኑ ከኢትዮጵያ ጋር የተለየ ግንኙነት እንዲኖራቸው ማድረጉንም ጋሽ አያልነህ ይገልጻሉ፡፡ ፑሽኪን የሩሲያ ዘመናዊ ሥነ ጽሑፍ ፈጣሪ እንደኾነ ይነገራል፤ የሩሲያ ዘመናዊ ሥነ ጽሑፍ ፈጣሪ የኢትዮጵያ ደም እንዳለው መነገሩ ለሀገራቱ ጥብቅ ግንኙነት እንዲፈጠር አድርጓል ባይ ናቸው፡፡

ሩሲያውያን በኢትዮጵያ የፈተና ዓመታት ሁሉ ከኢትዮጵያውያን ጋር መቆማቸውን ያስታወሱት ጋሽ አያልነህ በሶማሊያ ወረራ ወቅት ለኢትዮጵያ አጋዥ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ከዚያ ቀድመው በነበሩ የፈተና ጊዜያትም ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር እንደበረች አስታውሰዋል፡፡ በዚህ ዘመን በዓባይ ግድብ እና በሌሎች ጉዳዮች አንዳንድ ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ ፊታቸውን ሲያዞሩ ሩሲያ በወዳጅነቷ መቀጠሏን ተናግረዋል፡፡ የሩሲያውያን መልካም ወዳጅነት በሚገባው ልክ አለመነገሩንም አንስተዋል፡፡

ቋንቋ የባሕልና የዕውቀት መገለጫ ነው ያሉት ጋሽ አያልነህ አማርኛ ቋንቋ በሩሲያ ሀገር መሰጠት ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ እድገት አስተዋጽዖው የጎላ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ ተተርጉመው በሩሲያ ምድር ይነበቡ የነበሩ የአማርኛ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች በቀጥታ የመነበብ እድል እንደሚያገኙና የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ዓለማቀፋዊ እንዲኾን እንዳደረገውም ተናግረዋል፡፡ የአማርኛ ቋንቋ ታሪካዊ መኾኑ ተመራጭ እንዳደረገውም ገልጸዋል፡፡

የአማርኛ ቋንቋ በሌሎች ሀገራት መሰጠቱ ለሥነ ጽሑፉ እና ለደራሲያን አዲስ እድል ይዞ እንደሚመጣም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleእስካሁን የተዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ አፈጻጸም ዝቅተኛ መኾኑን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡
Next article“የደረሰውን የሰሊጥ ሰብል ለመሠብሰብ ከ1 ሚሊዮን በላይ የጉልበት ሠራተኛ ያስፈልጋል” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ግብርና መምሪያ