እስካሁን የተዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ አፈጻጸም ዝቅተኛ መኾኑን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

40

እስካሁን የተዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ አፈጻጸም ዝቅተኛ መኾኑን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

ባሕር ዳር: መስከረም 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዞኑ ከ13 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ቢያቅድም 64 ሺህ ሜትር ኪዩብ ብቻ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ችግር ለመቅረፍ የተፈጥሮ ማዳበሪያን እንደ አንድ አማራጭ ለመጠቀም እየተሠራ ነው፡፡ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን በምርት ዘመኑ ማዘጋጀት ከሚጠቅበት 13 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት አቅዶ ወደ ተግባር ገብቶ ነበር፡፡

ዞኑ በምርት ዘመኑ ለማዘጋጀት ካቀደው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ውስጥ 64 ሺህ ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያን ብቻ ማዘጋጀቱን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት የሥራ ሂደት መሪ አቶ ዮሃንስ ተስፋየ ገልጸዋል፡፡ የታቀደውን ያክል የተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ያልተቻለውም በአካባቢው ተፈጥሮ የነበረው የሰላም እጦት በምክንያትነት ቀርቧል፡፡

በላይ አርማጭሆ ወረዳ የከርከር ባለእግዚአብሔር ቀበሌ ተዘዋውረን ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች ወቅቱ ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ምቹ መኾኑን ነግረውናል፡፡ አርሶ አደሮቹ ወቅቱ ክረምት ያለፈበት እና ቅጠላ ቅጠል በሰፊው የሚገኙበት ወቅት በመኾኑ ለዝግጅቱ ምቹ ጊዜ ነው ብለዋል።

የተፈጥሮ ማዳበሪያ የመጠቀም ልምዳቸው እየዳበረ መምጣቱን የሚናገሩት አርሶ አደሮቹ በቀጣይ በስፋት ለማዘጋጀት እና ለመጠቀም እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡

በወረዳው በ2016 የሰብል ልማት ወቅት ከ7 መቶ 50 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ የተጥሮ አፈር ማዳበሪያ ለማዘጋጀት እየሠራ መኾኑን የወረዳው ግብርና ልማት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡ እስካሁንም 50 ሺህ ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ አፈር ማደበሪያ ተዘጋጅቷል ብሏል፡፡

ዘጋቢ፡- ደስታ ካሳ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አረንጓዴ ልማት ለቱሪዝም፤ ቱሪዝም ለአረንጓዴ ልማት”
Next article“የአማርኛ ቋንቋ በሩሲያ ሰማይ ሥር”