
ባሕር ዳር: መስከረም 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የዘመናዊው ዓለም አንዱ እና ሥልጡን የንግድ ዘርፍ እንደኾነ የሚነገርለት ቱሪዝም በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በምዕራብ አውሮፓ እንደተጀመረ ይነገርለታል፡፡
ቱሪዝም በዚህ ዘመን የሰው ልጅ ትርፍ ጊዜውን የሚያሳልፍበት የተዝናኖት አማራጭ ብቻ ሳይኾን ዘርፈ ብዙ ትውፊቶችም አሉት፡፡ የንግድ ልውውጥ፣ የባሕል መስተጋብር እና የእርስ በእርስ ትውውቅ የቱሪዝም በረከቶች ናቸው፡፡
የዘርፉ ሰዎች “ጪስ አልባው ኢንዱስትሪ” ሲሉ ይጠሩታል፡፡ ቱሪዝም መዳረሻው ሉላዊ ኾናለች በሚባልላት ዓለም ውስጥ ከአንደኛው አፅናፍ እስከ ሌላኛው ጫፍ ይዘረጋል፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ዘመን ተሻጋሪ የታሪክ አሻራ፣ መልከ ብዙ ባሕል እና ማራኪ መልካ ምድርን በተቸሩ ሀገራት ዘንድ ቱሪዝም የቱሪስቶች ቀልብ አንጠልጣይ የትምህርት፣ የትውውቅ እና የተዝናኖት አማራጭ ኾኗል፡፡
ቱሪዝም በዚህ ዘመን አይተኬ የእድገት መሰላል እና የምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ምሰሶ ነው ይባልለታል፡፡ ተፈጥሮን ከማዋከብ ወደ መንከባከብ፤ ከጭስ እና ብከላ ወደ ጽሞና የሚያሸጋግረው ቱሪዝም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በየዓመቱ በተለያዩ ዝግጅቶች እየታሰበ ይውላል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ44ኛ ጊዜ እና በኢትዮጵያ ደግሞ ለ36ኛ ጊዜ በመጪው መስከረም 17/2016 ዓ.ም ተከብሮ የሚውለው የዓለም ቱሪዝም ቀን በአማራ ክልልም በርእሰ መዲናዋ ባሕር ዳር ለ31ኛ ጊዜ ይከበራል ተብሏል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ “አረንጓዴ ልማት ለቱሪዝም፤ ቱሪዝም ለአረንጓዴ ልማት” በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበረው የዘንድሮው የቱሪዝም ቀን በኢትዮጵያ “ሰኔ እና ሰኞ” እንደሚሉት ከኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ጋር ተገናኝቷል ያሉን የአማራ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር መልካሙ አዳም ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አርአያ የኾነ የችግኝ ተከላ ሥራዎችን ሠርታለች የሚሉት ዳይሬክተሩ የተተከሉት ችግኞች በረጂም ጊዜ ለቱሪዝም እንቅስቃሴው መዳረሻ ከመኾን አልፈው ተመራጭ አካባቢን ይፈጥራል ብለዋል፡፡ ዘርፉ ምቹ ከባቢን ከመፍጠር ጋር የተቆራኘ በመኾኑ መሪ መልእክቱ በተለይም ለኢትዮጵያ ወቅታዊ እና ተስማሚ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ መስከረም 17/2014 ዓ.ም በከተማዋ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ የሚውለው የዓለም ቱሪዝም ቀን መዳረሻ የኾኑ ቦታዎችን በመጎብኘት እና በውይይት ይከበራል ብለዋል፡፡ በውይይቱም ከቱሪዝም እንቅስቃሴ እና ከመሪ ሃሳቡ ጋር በተያያዘ የመነሻ ጽሑፍ ቀርቦ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ይደረጋል ተብሏል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!