ባሕር ዳር፡- ጥር 14/2012ዓ.ም (አብመድ) በመላው ሀገሪቱ ያሉ ፖለቲከኞች ግጭት እንዳይቀሰቀስ እንዲሰሩ የጋሞ አባቶች ጠይቀዋል፡፡
ከአርባምንጭ ተነስተው መዳረሻቸውን ጎንደርን በማድረግ ጥምቀትን በጎንደር ታድመው፣ ስለፍቅርና አንድነት ሲመክሩ የሰነበቱት የጋሞ አባቶችና ወጣቶች ዛሬ ጥር 14/2012 ዓ.ም ባሕር ዳር ገብተዋል፡፡ ከሰዓት በኋላም ጣና ሐይቅ ውስጥ ከሚገኙት ገዳማት መካከል ሦስቱን ጎብኝተዋል፡፡
በጋሞ አባቶች ተምሳሌትነት የተደነቁ አምስት ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ከሠላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በመላው ሀገሪቱ ፍቅርን እንዲያስተምሩ መጠየቃቸውን የልዑኩ የመገናኛ ብዙኃን አስተባባሪ አቶ ተሻገር ጣሰው ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ሰላም እና አንድነትን የመስበክ አደራቸውን በተግባር ለመወጣት ከአንድ ሳምንት በኋላ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየዞሩ ለኢትዮጵያ አንድነት ማገር ለመሆን እንደሚሠሩ ቃል መግባታቸውን ነው አቶ ተሻገር የተናገሩት፡፡
በመላው ሀገሪቱ ያሉ ፖለቲከኞች ግጭት እንዳይቀሰቀስ እንዲሰሩ አባቶቹ መጠየቃቸውንም አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡
ልዑኩ ትናንት ጥር 13/2012 ዓ.ም የጎንደር እና የአርባምንጭ ከተማን የእህትማማችነት ሰነድ መፈራረሙ ታውቋል፡፡ የጋሞ አባቶችና ወጣቶች ነገ ጥር 15/2012 ዓ.ም ወደ አርባምንጭ ጉዞ እንደሚጀምሩ አቶ ተሻገር ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ