“በትምህርት ላይ ኢንቨስት ማድርግ ስለ ቀጣዩ ትውልድና ዓለም ኢንቨስት ማድርግ ነው” የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

69

ባሕርዳር፡ መስከረም 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የትምህርት ሚኒስትሩ እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ክቡር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአሜሪካ ኒውዮርክ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ተሳትፈዋል ።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባኤ ላይ የትምህርትን መሰረተ ልማት ማሻሻል የቀጣዩን ትውልድ የወደፊት እድል ማሻሻል መሆኑን ገልጸዋል።

መድረኩ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድህነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የማያቋርጥ ግጭትን እና አለመረጋጋትን ጨምሮ ውስብስብ ፈተናዎች ያሉበት በመሆኑ የ2030 የዘላቂ ልማት ግብ (SDG) አጀንዳ እና ሌሎች የጋራ ተግዳሮቶችን በዘላቂ ልማት ለመቅረፍ ሀገሮችን አንድ ለማድረግ ያለመ ነው።

በዚህም ሚኒስትሩ የተባበሩት መንግስታት ትምህርት በዲጅታል ዘመን ውስጥ ለልማት፣ ለፍትሃዊነት፣ ለሠላምና ለደህንነት የሚያግዝ ኢንቨስትመንት በሚል በኒውዮርክ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ተገኝተው ቁልፍ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በትምህርት ላይ በተደረገ የጎንዮሽ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር በትምህርት ላይ ኢንቨስት ማድርግ ስለ ቀጣዩ ትውልድና ዓለም ኢንቨስት ማድርግ ነው ያሉ ሲሆን እንደ ሀገርና መንግስት የተለያዩ ሪፎርሞችን በትምህርት ላይ እያካሄድን እንገኛለን ብለዋል።

አክለውም ከሌሎች በርካታ የአፍሪካ ሀገራት አንጻር ኢትዮጵያ ካላት ዓመታዊ በጀት 20 በመቶ ለትምህርት ሥራ እንደመደበች አንስተው ይህ የተመደበው በጀት መንግስት ካለው አቅም እና በትምህርት ዘርፉ ከሚስተዋለው ውስብስብ ችግር አንጻር በቂ ባለመሆኑ በዚህ ዓመት የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት ለማሻሻል ያለመ ‘ትምህርት ለትውልድ ‘ ሀገራዊ ነቅናቄ በመጀመር መላው ኅብረተስብ የብኩሉን ኀላፊነት እንዲወጣ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ትምህርት ስርዓት ውስጥ በርካታ ችግሮች ቢኖሩም ከዋና ዋና ችግሮች መካከል በትምህርት ቤቶች ምቹ የመማሪያ አካባቢ አለመኖሩ መሆኑን ገልጸው አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች መሰረታዊ የሚባሉት መሰረተ ልማቶች ንፁህ የመጠጥ ውኃ፣ ተገቢ የመጸዳጃ ቤት አገልግሎት፣ የቤተ ሙከራ እና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት የሚባሉትን መሰረታዊ መገልገያዎች የሌላቸው መሆኑን አብራርተዋል።

በመድረኩም ትምህርትን በመዋዕለ ነዋይ መደገፍ እስካልተቻለ ድረስ የዘላቂ ልማት ግቦችን ማሳካት ወይም እየተከሰቱ ያሉ ቀውሶችን መፍታት እንደማይቻል ተገልጿል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ሀገር አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ ሊካሄድ ነው።
Next article“አረንጓዴ ልማት ለቱሪዝም፤ ቱሪዝም ለአረንጓዴ ልማት”