ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ሀገር አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ ሊካሄድ ነው።

45

ባሕርዳር፡ መስከረም 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል “ግድቤን ለማጠናቀቅ ቃሌን አድሳለሁ” በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ ሊካሄድ መሆኑን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር ፍቅርተ ታምር፤ በዚሁ ጉዳይ ላይ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም “ግድቤን ለማጠናቀቅ ቃሌን አድሳለሁ” በሚል መሪ ሃሳብ ለአንድ ወር የሚቆይ ሀገር አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄው በሁሉም አካባቢዎች ከዛሬ ጀምሮ ለአንድ ወር የሚዘልቅ መሆኑን ጠቁመው፤ ለስኬቱ ሁላችንም የድርሻችንን እንወጣ ሲሉ ጠይቀዋል።

በዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር ከ500 እስከ 700 ሚሊየን ብር ለማሰባሰብ መታቀዱን ጠቅሰው፤ “ለግድባችን ሁለንተናዊ ድጋፋችን ይጠናከር” የሚል መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል።

4ኛውና የመጨረሻው ዙር የውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ በመጠናቀቁ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በድጋሚ እንኳን ደስ ያላችሁ የሚል መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል።

በ2016 ዓ.ም ለግድቡ ግንባታ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ለማሰባሰብ ታቅዷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በቀይ ባሕር አካባቢ የሚስተዋሉ የጸጥታ ሥጋቶችን በማስወገድ የቀጣናውን ደኅንነት ለማረጋገጥ በጋራ መሥራት ይገባል” ሌተናል ጄኔራል ዓለምሸት ደግፌ
Next article“በትምህርት ላይ ኢንቨስት ማድርግ ስለ ቀጣዩ ትውልድና ዓለም ኢንቨስት ማድርግ ነው” የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ