“በቀይ ባሕር አካባቢ የሚስተዋሉ የጸጥታ ሥጋቶችን በማስወገድ የቀጣናውን ደኅንነት ለማረጋገጥ በጋራ መሥራት ይገባል” ሌተናል ጄኔራል ዓለምሸት ደግፌ

62

ባሕርዳር፡ መስከረም 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በቀይ ባሕር አካባቢ የሚስተዋሉ የጸጥታ ሥጋቶችን በማስወገድ የቀጣናውን ደኅንነት ለማረጋገጥ በጋራ መሥራት እንደሚገባ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪና ተኩስ አመራር ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አለምሸት ደግፌ ገለጹ።

የቀይ ባሕር ቀጣና ደኅንነትና ጂኦ-ፖለቲካል ሁኔታን በተመለከተ በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩትና በኢፌዴሪ መከላከያ ዋር ኮሌጅ ትብብር የተዘጋጀ ውይይት እየተካሄደ ነው።

የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪና ተኩስ አመራር ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ዓለምሸት ደግፌ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የቀይ ባሕር ቀጣና ስትራቴጂካዊ የንግድና የፖለቲካ ማዕከል ነው።

የቀይ ባሕር ቀጣና ጂኦ-ፖለቲካ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸው ይህም የበርካታ ሀገራትን ትኩረት መሳቡን ገልጸዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን ቀጣናው ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሽብርተኝነትና መሰል የጸጥታ ሥጋቶችም የሚስተዋሉበት ነው ብለዋል።

በመሆኑም አሁን ላይ የቀጣናው የደኅንነት ሥጋት ከፍ እያለ መምጣቱን ነው ያስረዱት።

በመሆኑ እነዚህን ችግሮች ለመከላከል የቀጣናውን አገራት ትብብር ይፈልጋል ያሉት ሌተናል ጄኔራል አለምሸት የሀገራቱ የጋራ ትብብር ለቀጣናው ዘላቂ ሰላምና ልማት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የእስያና ፓስፊክ ሀገራት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ዶክተር ገበየሁ ጋንጋ፤ የቀይ ባህር ቀጣና አገራት በባህልና ሃይማኖት የተሳሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል።

የቀይ ባሕር ቀጣና በዓለም ካሉት ከፍተኛ የንግድ መስመሮች አንዱ በመሆኑ የአካባቢውን ጸጥታና ደኅንነት በጋራ በመጠበቅ ለጋራ ልማት ማዋል ይገባል ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር መሳፍንት ተፈራ፤ የቀይ ባሕር ቀጣና በኢኮኖሚ፣ ወታደራዊና መሰል ዓለም አቀፍ ጉዳዮች የጸጥታ ሥጋቱ እየተወሳሰበ መጥቷል ብለዋል።

በመሆኑም ለቀጣናዊ ችግሮች ቀጣናዊ መፍትሔ ለመስጠት የአካባቢው አገራት ሁለንተናዊ ትብብር ማድረግ እንዳለባቸው ነው ምክረ-ሃሳባቸውን የሰጡት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአቶ ደመቀ መኮንን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ገለጹ።
Next articleለሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ሀገር አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ ሊካሄድ ነው።