ዩናይትድ ኪንግደም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ወደ ስትራቴጂካዊ ትብብር ለማሳደግ እንደምትፈልግ ገለጸች።

40

ባሕርዳር፡ መስከረም 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዩናይትድ ኪንግደም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ ትብብር ለማሳደግ እንደምትፈልግ የዩናይትድ ኪንግደም የልማትና አፍሪካ ሚኒስትር አንድሪው ሚቼል ገለጹ። 78ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ “ሰላም፣ ብልጽግና፣ ለውጥና ዘላቂነት” በሚል መሪ ሀሳብ በኒው ዮርክ እየተካሄደ ነው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከጉባኤው ጎን ለጎን የዩናይትድ ኪንግደም የልማትና አፍሪካ ሚኒስትር አንድሪው ሚቼል ጋር ተወያይተዋል። አንድሪው ሚቼል አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትስስር ወደ ስትራቴጂክ ትብብር ደረጃ የማሳደግ ፍላጎት እንዳላት አመልክተዋል። ይህም እርምጃ በሁለቱ አገራት መካከል በንግድ፣ የኢንቨስትመንት ደህንነት፣ በስደተኞችና በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚያግዝ አመልክተዋል። ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ እ.አ.አ በሚያዚያ ወር 2024 በዩናይትድ ኪንግደም በሚካሄደው የአፍሪካ የኢንቨስትመንት ጉባኤ ላይ እንድሳተፍ መጋበዟን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ቁልፍ መልዕክአ ምድራዊ ቦታ ላይ የምትገኝና በአፍሪካ ወሳኝ ሚና የምትጫወት አገር መሆኗን አንስተዋል።

አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የኢንቨስትመንት ጉባኤ እንድትሳተፍ የቀረበላትን ጥያቄ እንደምትቀበልና የስትራቴጂካዊ ትብብር ፍላጎቱንም ኢትዮጵያ በመልካም ጎኑ እንደምታየው አመልክተዋል። በተጨማሪም በአገራዊና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ለአንድሪው ሚሼል ገለጻ ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በተያያዘም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከጉባኤው በተጓዳኝ ከአየርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክል ማርቲን ጋር ተወያይተዋል።

አቶ ደመቀ ኢትዮጵያና አየር ላንድ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን እንደገና የሚያድሱበት ወቅት አሁን ነው ብለዋል። ያለፈውን ምዕራፍ በመዝጋትና ትብብሩን ወደ ነበረበት ደረጃ በመመለስ አገራቱ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ትብብር እንደገና ማነቃቃት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሰላም ስምምነቱ በተመለከተ ገለጻ ያደረጉት አቶ ደመቀ ስምምነቱ በትክክለኛ አቅጣጫ እየሄደ እንደሚገኝና አየርላንድ የመልሶ ግንባታና መልሶ ማቋቋም ስራዎች እንድትደግፍ ጥሪ አቅርበዋል። የአየርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክል ማርቲን ኢትዮጵያ ጠቃሚ አጋር መሆኗንና አየርላንድ ለሁለቱ አገራት ሕዝቦች የረጅም ጊዜ ተጠቃሚነት እንደምትሰራ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Previous article“ከ51 ሺህ በላይ ከስደት ተመላሾች ሥልጠና ወስደው ወደ ሥራ ሊሰማሩ ነው” የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር
Next articleአቶ ደመቀ መኮንን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ገለጹ።