መንግሥት የሀገሪቱን ወቅታዊ  አሳሳቢ ሁኔታዎች ለይቶ እንዲያስተካክል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጠየቀ፡፡

432

በሰላማዊ መንገድ የመሰብሰብ እና የመደራጀት መብት በዋና ከተማዋ እና በክልሎች ውስጥ አልፎ አልፎ አላግባብ የመደናቀፍ ሁኔታ ስለተከሰተ መንግስት ማስተካከያ እንዲያደርግ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የሥራ ክንውን ሪፖርት ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡ በሪፖርቱም ኮሚሽኑን በአዲስ መልክ ለማዋቀርና ለማደራጀት እየተወሰዱ ስላሉት የሽግግር ወቅት የለውጥ እርምጃዎችና የአፈጻጸም ስልቶች ለምክር ቤቱ አስረድቷል፡፡ በተለይም የተቋሙን የአቅም ውስንነት ለማሻሻል፣ የሕግ ማዕቀፍ ክፍተቶችና ፈተናዎችን ለማስወገድ እየተዘጋጀ ስለሚገኘው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያ፣ ስለ አዲስ ኮሚሽነሮች አመራረጥ፣ እንዲሁም የኮሚሽኑ የበጀት እና የሰው ሃብት አስተዳደር ነፃነት አስፈላጊነት አብራርቷል፡፡ ስለ ወቅታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ እና ስጋት በአሁኑ ወቅት የተሟላ ሪፖርት ለማቅረብ እንዳልቻለ ለምክር ቤቱ የገለጸው ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ እርምጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ተጨባጭ ውጤቶች አስገኝቷል ብሏል፡፡

በለውጥ ሒደቱ የገጠሙት ውስብስብ እንቅፋቶች የሰብዓዊ መብት ቀውስ መፍጠራቸውን፣ በብሔር ማንነትና አልፎ አልፎም በሃይማኖት መስመር የተካረረ የፖለቲካ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፤ የአመጽ ግጭት እየቀሰቀሰ በከተማም በገጠርም፣ በጐዳናም በመንደርም በሆስፒታሎችና ትምህርት ቤቶች ሳይቀር ዜጐች በአሰቃቂ እና አስነዋሪ መንገድ ተገድለዋል፣ ተደፍረዋል፣ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ከመኖሪያቸው፣ ከሥራቸው፣ ከትምህርታቸው ተፈናቅለዋል፤ የሀገር ንብረትም ወድሟል ብሏል በሪፖርቱ፡፡

መሳሪያ የታጠቁ ቡድኖች ሰዎችን በኃይል አግተዋል፣ ገድለዋል፤ የመንግስት ሰራተኞች፣ ወንድና ሴት ወጣት ተማሪዎች እና ሕጻናት ሳይቀሩ የዚህ ሰለባ ሆነዋል ያለው ኮሚሽኑ የዚህ ሁኔታ መሠረታዊ ምክንያት የፖለቲካ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በመሆናቸው፣ መንግሥትና ምክር ቤቱ በተለይ ለፖለቲካዊ ችግሮች ለሀገር እና ለሕዝብ የሠላም ፍላጎት እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶች መከበር ላይ የተመሠረተ ሀገራዊ መፍትሔ ለመስጠት ትኩረት ሰጥቶ ጥረቱን ሊቀጥል ያስፈልጋል ብሏል፡፡

ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላው የምርመራ ሥራ አጥፊዎችን በሕግ ፊት ተጠያቂነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ሲል ያብራራው ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ አሁን ከምትገኝበት ልዩ የሽግግር ሁኔታ አንጻር ሰላምንና ደኅንነትን ማስፈን የሁሉንም ወገኖች ድርሻ ስለሚጠይቅ እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሰብዓዊ መብቶችን ማክበርና ማስከበር የመንግስት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጐች ኃላፊነት ስለሆነ በተለይ የፖለቲካ ድርጅቶችና መሪዎቻቸው ትልቅ ሚና እና ኃላፊነት አለባቸው ብሏል፡፡ ፖለቲከኞች የአመጽ ተግባሮችን በግልጽ በማውገዝና ደጋፊዎቻቸውን ወደ ሁከትና ብጥብጥ ከሚገፋፋ ተግባርና ንግግር ተቆጥበው በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እንዲሰሩም ጠይቋል፡፡

የአመጽ ግጭት በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ችግሩ እንዳይባባስ በመከላከልና አንጻራዊ ሠላምና መረጋጋት መልሶ በማስፈን በተለይ የፌዴራል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በሕይወት መስዋእትነት ጭምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በአንጻሩ አንዳንድ አካባቢዎች በፌዴራልም ሆነ በክልል የፀጥታ ኃይሎች የፀጥታ ማስከበር ሒደት ውስጥ ዜጐች ከሕግ ውጭ ለሞት፣ ለእስር እና እንግልት የተዳረጉበት ሁኔታም በመኖሩ የሕግና ሥርዓት ማስከበር ከፍተኛ አስፈላጊነት የመኖሩን ያህል በከፍተኛ ጥንቃቄና የኃላፊነት ስሜት ሊተገበር ያስፈልጋል ብሏል፡፡ በአዲሱ የፖለቲካ ምዕራፍ ከተሰጡት የማይረሱ ቃል ኪዳኖች ውስጥ አንዱ “ሳይጣራ እስር የለም” የሚለው ትክክለኛ የሕጋዊነት እና የሰብዓዊ መብት መርህ ነው፡፡ በአንዳንድ የወንጀል ሁኔታዎች እንዲሁም በበቂ ሕጋዊ ምክንያት በተወሰነ መልኩ ተጠርጣሪዎች በእስር ሆነው ጉዳዩ የሚጣራበት የሕግ አግባብ መኖሩ ቢታወቅም ዋነኛ የአሠራር መርሁ ከላይ እንደተገለጸው ከእስር በፊት ምርመራን በተሟላ መልኩ ማጠናቀቅ እና ከክስ ሒደት በፊት ያለውን የተጠርጣሪዎች እስር መከላከል ወይም በከፍተኛ መጠን መቀነስ እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል፡፡

በኢትዮጵያ በአዲስ መልክ ለተጀመረው ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ለውጥ ራዕይ ሰብዓዊ መብቶችና ነጻነቶችን ማክበርና ማስከበር የተልዕኮው ማስፈጸሚያ መሣሪያ ነው፡፡ ሆኖም በተለይ ከፖለቲካ ተሳትፎ መብት ጋር ተያያዥ የሆኑት ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በሰላማዊ መንገድ የመሰብሰብ እና የመደራጀት መብት ከዋና ከተማዋ ጀምሮ በክልሎችም ውስጥ አልፎ አልፎ አለአግባብ የመደናቀፍ ሁኔታ ስለተከሰተ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥት ኃላፊዎች ይህን አዝማሚያ አጥብቀው ሊከላከሉና ችግር ሲከሰትም የተፋጠነ መፍትሔ እንዲሰጡ ያስፈልጋል ብሏል ኮሚሽኑ በማብራሪያው፡፡

ኃላፊነት የጎደለው የመደበኛም ሆነ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም የጥፋት መሳሪያ ሊሆን ስለሚችል እና አሳሳቢ ምልክቶችም በመታየታቸው የሚዲያ ባለሙያዎች እና የማኅበራዊ ሚዲያ ዘጋቢዎችና ፀሐፊዎች በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እንዲሰሩ የጠየቀው ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ አዲሱን የለውጥ እርምጃ ዕውን ለማድረግ ልዩ እና ታሪካዊ ሚና ለነበራቸው ወገኖች የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ወዳጆች የሰጡት ተገቢ እውቅና እና አክብሮት እንደተጠበቀ ሆኖ ሊረሳ የማይገባው ሐቅ ይህ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያን በብዙ መልኩ ሰፊ መስዋእትነት የከፈሉበት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ድል እና ዕድል እንጂ የተወሰኑ ሰዎች ወይም ቡድኖች ብቻቸውን የፈጠሩት ወይም ለብቻቸው ባለቤት የሚሆኑበት አለመሆኑን አስገንዝቧል፡፡ በመሆኑም ሁሉም በእያንዳንዱ ግለሰብ ደረጃ ድሉንና እድሉን ሊጠብቅ፣ ችግሮችን በመተባበር እና በመተጋገዝ ሊቀርፍ፣ ሰላም ልማትና ዲሞክራሲ ለኢትዮጵያ ለማምጣት መብት እና ኃላፊነት አለበት ብሏል ኮሚሽኑ፡፡ ሁሉም ሰው ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶችን የማክበርና የማስከበር ግዴታና ኃላፊነት እንዳለበትም አስታውቋል፡፡

ምንጭ፡-የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን

Previous articleዩጋንዳ ዜጎቿ የአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ የምግብ እህል እንዲያከማቹ አስጠነቀቀች፡፡
Next articleየጋሞ አባቶችና ወጣቶች በመላ ሀገሪቱ በመዘዋወር ስለ ሀገር አንድነት እና ሰላም ሊሠሩ ነው፡፡