“ከ51 ሺህ በላይ ከስደት ተመላሾች ሥልጠና ወስደው ወደ ሥራ ሊሰማሩ ነው” የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

65

ባሕር ዳር: መስከረም 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከ51 ሺህ በላይ ከስደት ተመላሾች ሥልጠና በመስጠት ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መኾኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ከ37ሺህ በላይ ለኾኑ ዜጎች ከነቤተሰቦቻቸው የኑሮ ማሻሻያ ድጋፍ እንደተደረገላቸው ተገልጿል። በሚኒስቴሩ የሕገወጥ ሰዎች ዝውውር መከላከልና የተመላሽ ዜጎች ድጋፍና ክትትል መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ተግይበሉ በ2015 ዓ.ም በሁለት ዙሮች ከሳውዲ አረቢያ 134 ሺህ ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለስ ተችሏል። ከ51ሺህ በላይ የሆኑ ከስደት ተመላሾች ለሥራ የሚያስፈልጋቸውን ሥልጠና በመስጠት ወደ ሥራ እንዲሰማሩ እየተደረገ ነው።

ከስደት ከተመለሱት ውስጥ 6ሺህ የሚኾኑት ሕፃናት ናቸው። የተቀሩት ከ18 እስከ 35 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ዜጎች ናቸው ብለዋል አቶ ደረጀ። ከ51ሺህ በላይ የሆኑ ከስደት ተመላሾች ለሥራ የሚያስፈልጋቸውን ሥልጠና በመስጠት ወደሥራ እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል። ለስደት ተመላሽ ዜጎቹ ለሥራ መነሻ የሚሆን ካፒታልና የመሥሪያ ቦታ ተመቻችቶላቸዋል ነው ያሉት አቶ ደረጀ። በተለያዩ መስኮች ሥራ የጀመሩ ዜጎች መኖራቸውን ተናግረዋል። ዜጎቹ ተመልሰው ወደ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳይገቡ መንግሥት ሀገር ውስጥ ያሉ የሥራ ዕድሎችን በመጠቀም መለወጥ የሚችሉበትን ሁኔታ ሲያመቻች መቆየቱን አቶ ደረጀ አስታውሰዋል። ከስደት ተመላሽ ዜጎችን በማኑፋክቸሪንግ፣ በንግድ፣ በምግብ ዝግጅትና በተለያዩ ዘርፎች እንዲሰማሩ እየተደረገ መሆኑ ተጠቁሟል።

የቀጥታ ድጋፍ በማቅረብ የሴፍቲኔት ፕሮግራም ውስጥ እንዲካተቱ በማድረግ የቀጥታ የኑሮ ማሻሻያ ድጋፍ እንዲያገኙና በቋሚነት ወደ ሥራ ገብተው ራሳቸውን እንዲለውጡ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። አቅም ያላቸው ከስደት ተመላሾች በራሳቸው ወደ ሥራ ለመግባት ጥረት እያደረጉ ሲሆን፤ ከ37ሺህ በላይ የሆኑ ዜጎች ከነቤተሰቦቻቸው የኑሮ ማሻሻያ ድጋፍ እንደተደረገላቸው አስታውቀዋል። በተጨማሪ የሥነ-ልቦናና የአካል ጉዳት ችግር ደርሶባቸው ከፍተኛ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ከስደት ተመላሾች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ከገቡበት ችግር ውስጥ በፍጥነት ማገገም እንዲችሉ የተለያዩ የድጋፍና ክትትል ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።
እንደ አቶ ደረጀ ገለጻ፤ ከ160 በላይ የሚሆኑት ከስደት ተመላሾች በቲቢ በሽታ በመጠቃታቸው የተለየ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ኢፕድ ዘግቧል።

መዳረሻቸውን ደቡብ አፍሪካ በማድረግ ከደቡባዊ የኢትዮጵያ ክፍል የሚነሱና የጂቡቲን መስመር ይዘው መዳረሻቸውን ሳውዲ አረቢያና የመን አድርገው የሚንቀሳቀሱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች መኖራቸውን አመልክተው፤ የስደትን አስከፊነት የሚያስረዱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በተለያዩ አካባቢዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል። በተለይ በሆሳዕና ከተማ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መሪነት የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል የንቅናቄና ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ መካሄዱን አስታውሰዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕገወጥ የሰዎችን ዝውውር ለመከላከል የሚያስችላትን የሆሳዕና አዋጅ እየተባለ የሕግ ማዕቀፍ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሯን ተናግረዋል። በአካባቢው ይንቀሳቀሱ የነበሩ 153 ሕገወጥ የሰው ዝውውር ላይ የተሳተፉ ሰዎች ከንቅናቄው በኋላ ተይዘው ጉዳያቸው በሕግ እንዲያዝ መደረጉን አስታውቀዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየማኅበራዊ ሚዲያውን ዕድገት ተከትሎ ሀሰተኛ መረጃዎች በከፍተኛ ፍጥነት እየተሠራጩ መሆኑ ተገለጸ።
Next articleዩናይትድ ኪንግደም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ወደ ስትራቴጂካዊ ትብብር ለማሳደግ እንደምትፈልግ ገለጸች።