
ባሕር ዳር: መስከረም 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በእድገት ላይ የሚገኙ ሀገራት መሠረታዊ ችግሮች ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ የውጭ ምንዛሬ እጥረት አንዱ ነው።
የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍ በቂ ምርት አምርቶ ወደ ውጭ መላክ እና ከውጭ የሚገባውን ምርት ደግሞ በሀገር ውስጥ አምርቶ መተካት ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡
በቀጣይ ሦስት ዓመታት ከውጭ የሚገቡትን በሀገር ውስጥ ለመተካት ትኩረት ከተሠጣቸው ምርቶች ውስጥ ስኳርና ዘይት ቀዳሚዎቹ መኾናቸውን የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ከዚህ በፊት ለአሚኮ መግለጹ ይታወሳል፡፡
የቢሮው መረጃ እንደሚያሳየው የአማራ ክልል ወርሃዊ የዘይት ፍጆታ እስከ 10 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ይደርሳል፡፡ በክልሉ ከሚገኘው የዘይት ፋብሪካዎች ውስጥ የ‹‹ፌቤላ›› ዘይት ፋብሪካ ብቻ በቀን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት የማምረት አቅም አለው። እንደ ደብሊው ኤ፣ ቋሪት አግሮ፣ ዩኒሰን እና ሌሎች የዘይት ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ወደ ማምረት ቢገቡ ደግሞ ከውጭ የሚገባውን ዘይት በመተካት ለግዥ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት ይቻላል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር አግደው ሞላ እንዳሉት በ2015/2016 የምርት ዘመን ክልሉ በምግብ ራስን ለመቻል ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ባለፈ ለኢንዱስትሪዎች ጥሬ እቃ ማቅረብ እና ገበያ ተኮር ሰብሎችን ማምረት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ይገኛል፡፡
በምርት ዘመኑ በዘር ከተሸፈነው 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 802 ሺህ 300 ሔክታር መሬት በሰሊጥ፣ አኩሪ አተር እና ማሾ ተሸፍኗል፡፡ ከ14 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርትም ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አጠቃላይ በክልሉ በ2015/2016 ዓ.ም የምርት ዘመን ይገኛል ተብሎ ከታቀደው 160 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ውስጥ ደግሞ ከአስር የ‹‹ኮሞዲቲ›› ሰብሎች ከ55 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታቅዷል፡፡
ቢሮው የገበያ ችግር እንዳያጋጥም ከአምራቾች ፣ከኢንዱስትሪዎች ፣ከኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ እና ከሚመለከታቸው የፌደራል እና ሌሎች አጋር አካላት ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት ቅድመ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ የኢንዱስትሪ ባለቤቶችም ምርቱን በወቅቱ በመረከብ አምራቹን ሊያበረታቱ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በ2014/2015 ዓ.ም የምርት ዘመን በአኩሪ አተር እና ማሾ ላይ የተከሰተው የገበያ ትስስር ችግር እና የግብርና አምራች እና ግብአት አቅራቢ ግንኙነት (ኮንትራት ፋርሚንግ) ውጤታማ አለመኾን በአምራቾች ላይ ቅሬታ መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በምርት ዘመኑ አምራቾች በሌሎች ሰብሎች ላይ እንዲያተኩሩ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!