“ኢትዮጵያ የኒውክሌር ኢነርጂን ለሰላማዊ ዓላማ ለመጠቀም ከሩሲያ ኩባንያዎች ጋር እየሠራች ነው” የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

85

ባሕር ዳር: መስከረም 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኢትዮጵያ የኒውክሌር ኢነርጂን ለሰላማዊ መስክ ለመጠቀም የምታደርገው ጉዞ የተሳካና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ከሩሲያ ኒውክሌር ኢነርጂ ኩባንያዎች ጋር እየሠራች መሆኗ ተገልጿል፡፡

የኒውክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከልንና ብሔራዊ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ በኢትዮጵያ ለመገንባትና የኢትዮጵያን ብሔራዊ የኒውክሌር መሠረተ ልማት ለማልማት እየተሠራ ነው፡፡

በዚህም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከሩሲያ ሮሳቶም ኒውክሌር ኢነርጂ ኩባንያ ኃላፊዎች ጋር በአዲስ አበባ እየመከረ ነው፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደስታ አበራ ከሮሳቶም ጋር በመሥራት የእውቀት፣ የልምድ እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳለጥ ወደ ኒውክሌር ኢነርጂ ፕሮግራም ለሚደረገው ጉዞ መሠረት ነው ብለዋል፡፡

እንዲሁም ሥራው ደህንነቱ የተጠበቀ እና አካባቢን ያገናዘበ እንዲሆን በሁለትዮሽ ትብብር መሠራቱ ቅድሚያ የተሰጠው ተግባር ነው ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ለሁለት ቀናት የሚቆየው መድረክ ከሩሲያ ኒውክሌር ኢነርጂ ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎች ሰፊና ጥልቅ የሆነ የእውቀት ቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል።

በሰላማዊ መንገድ አቶሚክ ኢነርጂ ግንባታና አጠቃቀም ላይ የተደረገው የሁለትዮሽ ትብብር በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከሚያደርገው አስተዋጽኦ ባሻገር የኢትዮጵያ-ሩሲያ ግንኙነት ይበልጥ እያጠናከረው እንደሚሄድ ተጠቁሟል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በሞስኮ መሰጠት ጀመረ።
Next article“በምርት ዘመኑ በምግብ ራስን መቻል ፣ ለኢንዱስትሪዎች ጥሬ እቃ ማቅረብ እና ገበያ ተኮር ሰብሎች ላይ ትኩረት ተደርጓል” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ