
ባሕር ዳር፡- ጥር 14/2012ዓ.ም (አብመድ) ከፍተኛ መጠን ያለው የአንበጣ መንጋ ከኬንያ ወደ ዩጋንዳ እየተጠጋ እንደሆነ ተሰምቷል፡፡
የአንበጣ መንጋው በዩጋንዳ ሰሜን ምስራቃዊ አቅጣጫ በሚገኙት ሳምቡሩ እና ቱርካና የተባሉ የኬንያ አካባቢዎች ተከስቷል፡፡ የሀገሪቱ መንግሥትም ጉዳት ከማድረሱ በፊት ለመከላከል በተጠንቀቅ ላይ መሆኑን ገልጧል፡፡ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሩሃካና ሩጉንዳ ትናንት እንደገለጹት የአንበጣ መንጋው በሁሉቱ ሀገራት የጋራ ድንበር ላይ መታየቱ ለሀገሪቱ ከፍተኛ ሥጋት ፈጥሯል፡፡
የመከላከሉን ተግባር ውጤታማ ለማድረግም ከሥራው ጋር ግንኙነት ያላቸው ስምንት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በቅንጅት አንዲሠሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዝዘዋል፡፡ ለድንገተኛ አደጋ መከላከል ጥሪው ሁሉም ተቋማት እንዲዘጋጁም ነው ሩጉንዳ ጥሪ ያቀረቡት፡፡ የአንበጣ መንጋውን በጋራ ለመከላከል ከኬንያ መንግሥት ጋር እየተነጋገሩ እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
የአንበጣ መንጋው የመከላከል ሥራውን አሸንፎ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል የሀገሪቱ ዜጎች ለአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ የምግብ እህል እንዲያከማቹም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡ የሀገሪቱ የዘርፉ ተመራማሪዎችም የአንበጣ መንጋው በሰብል እና በእፅዋት ላይ ጉዳት በማድረስ ርሃብ እንዲከሰት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡
የመከላከሉን ሥራ የማስተባበርና በጀቱንም የመሸፈን ድርሻ የተሰጠው የሀገሪቱ ግብርና ሚኒስቴርም ለጸረ ተባይ መድኃኒት፣ በመከላከሉ ሥራ ለሚሰማሩ አውሮፕላኖች ነዳጅ እና ተያያዥ ወጪዎች 1 ነጥብ 35 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያስፈልገኛል ብሏል፡፡ የሀገሪቱ የግብርና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በዩጋንዳ ለመጨረሻ ጊዜ የአንበጣ መንጋ የተከሰተው ከ70 ዓመታት በፊት ነበር፡፡ በወቅቱም በሰብል ምርቷ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን አስታውሷል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ እና እርሻ ድርጅት ያወጣው መረጃ እንደሚያመላክተው አንድ በጣም አነስተኛ የአንበጣ መንጋ በአንድ ቀን እስከ 35 ሽህ ሰዎችን ሊመግብ የሚችል ሰብል ያወድማል፡፡
ምንጭ፡- ሲ ጂ ቲ ኤን አፍሪካ
በአስማማው በቀለ