
ጎንደር: መስከረም 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በጎንደር ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ተማሪዎች የጎንደር ዩኒቨርሲቲ 300 ሺህ ብር የሚያወጡ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን የዩኒቨርሲቲው የአሥተዳደር እና ቢዝነስ ልማት ዋና ዳይሬክተር ዓለማቀፍ ዋኛው ገልጸዋል።
አሁን የተደረገው ድጋፍም 300 ሺህ ብር የሚያወጣ የትምህርት ቁሳቁስ እንደኾነ ገልጸው ከ400 በላይ ለሚኾኑ ተማሪዎች ድጋፍ መደረጉን አስረድተዋል፡፡
በቀጣይም ከድጋፍ ባለፈ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚቋቋሙበት ሥራ እንደሚሠራ ነው የተናገሩት።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አትንኩት ጌታቸው እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች በመደገፍ በኩል ውጤታማ ሥራዎችን እየሠራ ነው።
በከተማ አሥተዳደሩ በኩልም ኮሚቴ በማቋቋም ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ለማድረግ እየተሠራ እንደኾነም አብራርተዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው የተማሪ ወላጆች የተደረገው ድጋፍ ለቀጣይ የትምህርት ዘመን የሚገጥማቸውን የኢኮኖሚ ጫና እንደሚያቃልልላቸው ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- ዳንኤል ወርቄ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!