
ባሕርዳር፡ መስከረም 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረታቦር ከተማ ማኅበረሰብ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቆም ለሰላም እየሠራ መኾኑን የከተማ አሥተዳደሩ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ገልጿል። የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ሹመት በላቸው የደብረታቦር ሕዝብ ሰላም እና ልማት ወዳድ ነው፤ ሰላሙን የሚያደናቅፍበት አካል ሲከሰትም በጋራ ቆሞ የሚከላከል ነው ብለዋል።
ደብረታቦር ከተማ አሁን ላይ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደምትገኝም ኀላፊ ተናግረል። በከተማው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ ፖሊስ እና የሚሊሻ አባላት በመቀናጀት የማኅበረሰቡን ሰላም እያስጠበቁ እንደሚገኙም አቶ ሹመት ተናግረዋል።
ሕዝቡም ባለፈው ተከስቶ የነበረው የሰላም መደፍረስ እንዳይደገም እና አሁን ላይ የተገኘው ሰላም ዘላቂ እንዲኾን ከጸጥታ አካላሉ ጎን በመቆም የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የደብረታቦር ከተማ ማኅበረሰብ በአንድነት ሰላሙን በማስጠበቅ ረገድ ሰፊ ልምድ እንዳለውም አቶ ሹመት አንስተዋል። ተከስቶ የነበረው የሰላም እጦት በፍጥነት ተፈትቶ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር ተከታታይ ሕዝባዊ ውይይቶች ስለመደረጋቸውም ተናግረዋል።
ሰላምን ሊያደፈርሱ የሚችሉ ኹኔታዎችን በመለየት በቅንጅት ለመፍታት የማኅበረሰቡ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ መግባባት ላይ ተደርሶ በጋራ እየተሠራ ነውም ብለዋል። ”ከግጭት የሚገኝ ትርፍ የለም” ያሉት ኀላፊው የከተማዋ ሰላም እንዲመለስ ያስቻሉ ነዋሪዎቿን አመስግነው አኹናዊው የተረጋጋ ሰላም ዘላቂ እንዲኾንም በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ መልእክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!