“በሰሜን ጎንደር ዞን የዝናብ እጥረት በተከሰተባቸው ወረዳዎች 452 ሺህ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል” የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት

60

ባሕርዳር፡ መስከረም 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎንደር ዞን የዝናብ እጥረት በተከሰተባቸው ወረዳዎች ነዋሪዎቹ ለችግር መጋለጣቸውን የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሰላምይሁን ሙላት በዞኑ ጃናሞራ፣ በየዳ፣ ምሥራቅና ምዕራብ ጠለምት ወረዳዎች የዝናብ እጥረት መከሰቱን ገልጸዋል፡፡ አካባቢው በጦርነት ክፉኛ የተጎዳ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው ከጦርነት ጉዳት ለመውጣት በሚሠራበት ጊዜ የዝናብ እጥረት መከሰቱን ነው ያነሱት፡፡ የዝናብ እጥረት በተከሰተባቸው ወረዳዎች ዝናብ ያልዘነበባቸው ቀበሌዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡

የዝናብ እጥረት መከሰት በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉንም አመላክተዋል፡፡ እናቶች እና ሕጻናት በዝናብ እጥረቱ ምክንያት ለችግር መጋለጣቸውንም አንስተዋል፡፡ በዞኑ የዝናብ እጥረት በተከሰተባቸው ወረዳዎች 452 ሺህ ወገኖች ለችግር መጋለጣቸውንም ተናግረዋል፡፡ 202 ሺህ የሚኾኑት ደግሞ አስቸኳይ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት፡፡ ዝናብ ባልዘነበባቸው አካባቢዎች የምግብ እና የንጹሕ መጠጥ ውኃ እጥረት መኖሩንም አመላክተዋል፡፡ የጤና ችግር መከሰቱንም ገልጸዋል፡፡ የዝናብ እጥረት በተከሰተባቸው አካባቢዎች በርካታ እንስሳት መጎዳታቸውንም ተናግረዋል፡፡

ዞኑ በዝናብ እጥረት የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት ጥረት ማድረጉን ያነሱት ኀላፊው የተፈጠረው ችግር ግን ከዞኑ አቅም በላይ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ሚዲያዎች በችግር ላይ ያሉ ወገኖች ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስባቸው እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን ለመታደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ሕዝቡ፣ መንግሥትና አጋር አካላት በችግር ውስጥ ላሉ ወገኖች ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባቸውም ገልጸዋል፡፡ በዝናብ እጥረት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች በርብርብ ድጋፍ ማድረግ ካልተቻለ በረሃብ ምክንያት የምናጣቸው ወገኖች ይኖራሉ ነው ያሉት፡፡ የክልሉ መንግሥት እያደረገው ያለው ድጋፍ የሚመሰገን ቢኾንም በቂ አለመኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የተጠናከረና በቂ የኾነ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

የሰበዓዊ ተቋማት ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የተጎጂዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም አመላክተዋል፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር ብርሃኑ ዘውዱ በክልሉ በሰሜን ጎንደር፣ በማዕከላዊ ጎንደር፣ በደቡብ ጎንደር እና በዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የዝናብ እጥረት ያጋጠማቸው አካባቢዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ ዝናብ ዘግይቶ በገባባቸውና ባቋረጠባቸው አካባቢዎች ችግር መፈጠሩንም ተናግረዋል፡፡

ክልሉ ያለውን ተጠባባቂ የሰብዓዊ አቅርቦት ችግር ለገጠማቸው አካባቢዎች መላኩንም አመላክተዋል፡፡ የተላከው ድጋፍ በቂ አለመኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ ችግሮችን በመለየት ቀጣይ እርምጃዎችን ለመውሰድ እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ወደፊት በሚኖረው የምርት ግምገማ አሁን ካሉት በተጨማሪ ሌሎች አካባቢዎችም ችግር ሊኖር እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡ በክልሉ በዝናብ እጥረት ምን ያክል ወገኖች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ወደ ፊት በሚደረግ ጥናት እንደሚታወቅም ተናግረዋል፡፡ የእንስሳት መኖ የሚያስፈልጋቸውን ከእንስሳት ሃብት ልማት ጋር እየተነጋገሩ ድጋፍ ለማድረግ እየሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡ የሚደረገውን ጥናት መሠረት በማድረግ ምላሽ እንደሚሰጥም ገልጸዋል፡፡ አፋጣኝ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸውም ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ነው የተናገሩት፡፡

በሰሜን ጎንደር ዞን የዓለም የምግብ ፕሮግራም ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር ያስታወሱት ዳይሬክተሩ ድጋፉ በመቆሙ ምክንያት ችግር መፈጠሩን ነው የገለጹት፡፡ ችግር ያለባቸውን ወገኖች ለመለየት የጋራ ልየታ እየተደረገ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ልየታው እንደተጠናቀቀ ሃብት እንደሚጠየቅም ገልጸዋል፡፡ በአካባቢው ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ ተቋማትም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዓባይ፣ በቆቃ እና በአዋሽ ተፋሰስ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡
Next article”የደብረታቦር ከተማ ነዋሪዎች ከጸጥታ አካላት ጋር በመኾን ለሰላም እየሠሩ ነው” የከተማ አሥተዳደሩ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ