“በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ከሚከናወኑ ተግባራት በተጓዳኝ ለግብርና ልማት በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው” ዶክተር ድረስ ሳህሉ

53

ባሕርዳር፡ መስከረም 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ከሚከናወኑ ተግባራት በተጓዳኝ ለግብርና ልማት ሥራዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን በምክትል ርዕሠ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ገለጹ።

ዶክተር ድረስ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በአማራ ክልል የተፈጠረውን የሰላም ችግር ተከትሎ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ጫና ማሳደሩን ተናግረዋል።

በዚህም በተለይ የግብርናው ዘርፍ ከእርሻ ሥራ እስከ ግብዓት አቅርቦት ሲፈተን መቆየቱን አንስተው፤ በክልሉ ተግባራዊ የተደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ በበርካታ አካባቢዎች መደበኛ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም አዳዲስ አመራሮችን እስከታችኛው መዋቅር መልሶ በማደራጀት የጋራ ዕቅድ በማውጣት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አዲሱ የክልሉ አመራር ሰላም ማስፈንና የልማት ሥራዎችን ማፋጠን ላይ ቀዳሚ ትኩረት እድርጎ እየሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ክልሉ ሰፊ የግብርና ልማት የሚከናወንበት መሆኑን ያነሱት የቢሮ ኃላፊው፤ በፀጥታ ችግር የተስተጓጎለውን የልማት ስራ ለማካካስ የተቀናጀ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የግብርና ልማት ባለሙያዎችም ከአርሶ አደሩ ጋር በመሆን እየሠሩ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ በክልሉ ርጥበት በሚቀጥልባቸው አካባቢዎች የሚለሙ ሰብሎች የማሳ ዝግጅት እና የበጋ መስኖ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የሰብሉን እድገት ጤናማና ምርታማ ለማድረግ የዩሪያ ማዳበሪያ በበቂ ሁኔታ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ እንደሚገኝም ተናገረዋል።

ከዚህም ባለፈ በቀሪዎቹ ርጥበታማ ወቅቶች ለሚዘሩ ሰብሎች የሚያገለግል የግብዓት አቅርቦት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ወደ ክልሉ እየገባ እንደሚገኝ ነው ዶክተር ድረስ ሳህሉ የጠቀሱት።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ነሐሴ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ አቶ አረጋ ከበደን የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር አድርጎ መሾሙ ይታወቃል።

ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ በተደራጁ አራት ኮማንድ ፖስት እየተከናወኑ የሚገኙ የሰላም ማስከበር ሥራዎች ዙሪያ ከክልሉ አዲስ አመራር ጋር መወያየታቸው ይታወቃል።

በውይይቱም በክልለ ዘላቂ ሰላመ ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የሕዝብን የልማት ጥያቄ በአፋጣኝ ለመመለስ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ ገልጸው ነበር።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበፀጥታ ችግር ምክንያት የተቋረጠውን ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ገቡ።
Next articleበዓባይ፣ በቆቃ እና በአዋሽ ተፋሰስ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡