
በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ማርቆስ ከተማ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሽዋ በር ቅርንጫፍ ሰራተኞች ጥር 12/2012 ዓ.ም ደንበኞቻቸውን ያስተናግዳሉ፡፡
ረዳት ሳጅን ስማቸው ቢሻው የሚያወጣው ገንዘብ በዛ ያለ በመሆኑ የባንኩ ሰራተኞች ወደ ውስጥ እንዲገባ ያደርጉታል፡፡ በሥራ የተወጠረው የባንኩ አካውንታንትም ግለሰቡ ከጠየቀው 243 ሽህ ብር ላይ 100 ሺህ ብር ጨምሮ 343 ሺህ ብር ይሰጠዋል፡፡
ረዳት ሳጅን ስማቸውም የተቀበለው ከራሱ ላብ ውጭ የሆነ ገንዘብ መሆኑን ሲያረጋግጥ ገንዘቡን ለባንኩ መመለሱን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደብረማርቆስ ሸዋ በር ቅርንጫፍ ዋና ሥራ አስኪያጅ ደንበሩ ተፈራ ለአብመድ ተናግረዋል፡፡
ሥራ አስኪያጁ እንደገለጹት ረዳት ሳጅን ስማቸው የፈጸመው ተግባር ቅንነት የተሞላበት በመሆኑ ሊመሰገን እንደሚገባው ነው። ለግለሰቡ የምስጋና የምስክር ወረቀት መስጠታቸውንም ተናግረዋል፡፡
ረዳት ሳጅን ስማቸውም ስለተሰጠው የምስጋና የምስክር ወረቀት አመስግኗል፤ ደግነት ለራስ እንደሆነም ተናግሯል፡፡
ገንዘቡን ሲመልስ ያዩት የከተማዋ ነዋሪዎችም ረዳት ሳጅን ስማቸው የሠራው በጎ ተግባር ከአንድ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅና የሚያስመሰግን መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
ዘጋቢ፡-ምሥጋናው ብርሃኔ