በፀጥታ ችግር ምክንያት የተቋረጠውን ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ገቡ።

80

ጎንደር፡ መስከረም 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በፀጥታ ችግር ምክንያት የተቋረጠውን ፈተና የሚወስዱ ከ11 ሺህ 581 በላይ ተማሪዎችን በተረጋጋ መልኩ ለማስፈተን ዝግጅት ማድረጉን ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ገለጸ፡፡ በፀጥታ ችግር ምክንያት የተቋረጠውን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና የሚወስዱ በማዕከላዊ ጎንደር፣ በምዕራብ ጎንደር፣ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን እና በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ ተማሪዎች ፈተናቸውን ለማጠናቀቅ በድጋሚ ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ገብተዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ አቶ ዳንኤል ውበት 3 ሺህ 134 ፈተናውን የሚወስዱ ተማሪዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱን እና በቂ የሥነ ልቦና ዝግጅት እንዲኖራቸው መሠራቱንም ተናግረዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ አቶ ክንዱ ዘውዱ ተማሪዎች ዝግጅት እንዲያደርጉ ቀደም ብሎ መሠራቱን ገልጸዋል። ተፈታኝ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ በሚጓዙበት ወቅት የመጓጓዣ ኹኔታ ምቹ እንዲኾን መሠራቱንም አመላክተዋል። በዞኑ 6 ሺህ 119 ተፈታኝ ተማሪዎች መኖራቸውንም ኀላፊው አንስተዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአሥተዳደር እና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ልጅዓለም ጋሻው በሶስት ዞኖችና በጎንደር ከተማ የሚገኙ ከ11 ሺህ 581 በላይ ተማሪዎች በተረጋጋ ኹኔታ ፈተናቸውን እንዲያጠናቅቁ ዩኒቨርሲቲው በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል። ያነጋገርናቸው ተፈታኝ ተማሪዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት ፈተናቸውን ማጠናቀቅ አለመቻላቸውን በማስታወስ በአሁኑ ወቅት ፈተናውን ለመውሰድ ሙሉ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል። ተማሪዎቹ ያቋረጧቸውን የኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂ እና ሲቪክስ የትምህርት አይነቶችን ፈተና የሚወስዱ ይኾናል።

ዘጋቢ፡- ቃልኪዳን ሀይሌ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በዝናብ እጥረት ምክንያት በዚህ የምርት ዘመን ሦስት ቀበሌዎች ምርት አይኖራቸውም” የምሥራቅ በለሳ ወረዳ
Next article“በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ከሚከናወኑ ተግባራት በተጓዳኝ ለግብርና ልማት በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው” ዶክተር ድረስ ሳህሉ