“በዝናብ እጥረት ምክንያት በዚህ የምርት ዘመን ሦስት ቀበሌዎች ምርት አይኖራቸውም” የምሥራቅ በለሳ ወረዳ

64

ባሕርዳር፡ መስከረም 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በተደጋጋሚ ባጋጠመው የዝናብ እጥረት በርካታ ወገኖች ለችግር መጋለጣቸውን በማእከላዊ ጎንደር ዞን የምሥራቅ በለሳ ወረዳ አስታውቋል፡፡

የምሥራቅ በለሳ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ ሽፈራው ማሞ በርካታ ወገኖች በዝናብ እጥረት ምክንያት ችግር ላይ መውደቃቸውን ገልጸዋል፡፡ በወረዳው እስከ ሐምሌ 24/2015 ዓ.ም ድረስ ዝናብ ሳያገኙ የቆዩ ቀበሌዎች እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ በወረዳው ከሚገኙ 30 ቀበሌዎች መካከል ሰኔ አጋማሽ ላይ ዝናብ ያገኙት 12 ቀበሌዎች ብቻ ናቸው፡፡ በተለይም ሦስት ቀበሌዎች እስከ ሐምሌ 24/2015 ዓ.ም ድረስ ዝናብ ሳያገኙ ቆይተዋል፡፡

በወረዳው የተከሰተው የዝናብ እጥረት ባለፈው የምርት ዘመን ጀምሮ ችግር መፍጠሩን ነው የተናገሩት፡፡ ማኅበረሰቡ ከባለፈው ዓመት ጉዳት ሳያገግም ለሌላ ችግር መጋለጡን አስታውቀዋል፡፡ ሦስቱ ቀበሌዎች ምንም ዓይነት ምርት እንደማይኖራቸውም ገልጸዋል፡፡ ነዋሪዎቹ እንስሳቶቻቸው ጉዳት እንዳይደርስባቸው ወደ አጎራባች ወረዳዎች መውሰዳቸውንም ተናግረዋል፡፡ ብዙዎቹ ቀያቸውን ለቀው የጉልበት ሥራ ሊሠሩ አካባቢያቸውን ለቀው መሄዳቸውን አንስተዋል፡፡

በተደጋጋሚ የተጠየቀው ለእንስሳት መኖ እና ለነዋሪዎች ድጋፍ በጊዜ አለመድረሱንም ገልጸዋል፡፡ በወረዳው በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች በችግር ላይ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ የወረዳውን ነዋሪዎች የዝናብ እጥረት በተደጋጋሚ ጉዳት እያደረሰባቸው መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡ አፋጣኝ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ ከ68 ሺህ በላይ ወገኖች አስቸኳይ የሰበዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፍልጋቸውም አስታውቀዋል፡፡

በዝናብ እጥረት የተጎዳውን ማኅበረሰብ የኑሮ ውድነቱ ተጨማሪ ችግር እንደኾነበትም አመላክተዋል፡፡ አሁን ላይ በወረዳው ዝናብ ማቆሙንም ገልጸዋል፡፡

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት የአደጋ መከላል ተወካይ ቡድን መሪ አረጋልኝ ሰውአገኝ በዞኑ ምሥራቅ በለሳና ኪንፋዝ በገላ ወረዳዎች በዝናብ መዝግየት ምክንያት ችግር እንደተፈጠረ ተናግረዋል፡፡ በሁለቱ ወረዳዎች አፋጣኝ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፍ እያደረጉ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች የተውጣጣ ኮሚቴ የዳሰሳ ጥናት አካሂዶ የሚያስፈልገውን መለየቱንና ለክልል ማሳወቁንም ተናግረዋል፡፡ ክልሉም የአስቸኳይ ድጋፍ ፈቅዷል ነው ያሉት፡፡ በቀጣይ በሚኖረው የምርት ግምገማ ምን ያክል ወገኖች ምርታቸው ይቀንሳል ፣ምን ያክሉስ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል የሚለው እንደሚለይም አመላክተዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ጀምሮ ተደጋጋሚ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ቅድሚያ እንደሚሰጣቸውም ተናግረዋል፡፡ አሁን የሚደረገው ድጋፍ በቂ አለመኾኑን ያነሱት ቡድን መሪው በቀጣይ በሚኖረው ጥናት እየተለየ ድጋፍ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡ በየቀኑ በሚኖረው ግምገማ ሰው እንዳይጎዳ እንደሚሠራም አመላከተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የዋግኽምራ ሕዝብ ሕግና ሥርዓትን አክብሮ የሚያስከብር የሰላም ተምሳሌት ነው” የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ
Next articleበፀጥታ ችግር ምክንያት የተቋረጠውን ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ገቡ።