“የዋግኽምራ ሕዝብ ሕግና ሥርዓትን አክብሮ የሚያስከብር የሰላም ተምሳሌት ነው” የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ

45

ባሕር ዳር: መስከረም 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሁሉም አካባቢዎች ከወቅታዊ የሰላም እጦት ችግር የፀዱ ስለመኾናቸው ተገልጿል፡፡ የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ አዘዘው አዳነ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሕዝብ ሀገር ለማጽናት በተደረገው ሀገራዊ ጦርነት ብዙ መስዋእትነት የከፈለ እና የሰላምን ፋይዳ ጠንቅቆ የሚረዳ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረው የሰላም እጦት በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደርም እንዳይከሰት ያደረገው ሕዝቡ ለሰላሙ ዘብ በመቆሙ ምክንያት ነው ብለዋል።

የዋግ ኽምራ ሕዝብ በርካታ ጥያቄዎች ያሉት ቢኾንም ሕግ እና ሥርዓትን ተከትሎ ይጠይቃል እንጅ ወደ አላስፈላጊ እና የማያተርፍበት ጦርነት ከቶውንም አይገባም ሲሉ ተናግረዋል። “የዋግ ሕዝብ ሕግና ሥርዓትን አክብሮ የሚያስከብር የሰላም ተምሳሌት ነው” ሲሉ ነው ኀላፊው የገለጹት።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰላምን የሚያደፈርሱ ምልክቶች ተስተውለው እንደነበር የገለጹት ኀላፊው የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሕዝብ በመቀናጀት እና በስሌት በመንቀሳቀሱ ምክንያት ሰላሙን አስጠብቋል ብለዋል። “የዋግ ሕዝብ በጦርነት ብዙ ከፍሏል” ያሉት መምሪያ ኀላፊው ሕዝቡ ከጦርነት ዳፋ ለመውጣት የሚታትር እንጅ ወደ ዳግም ጦርነት ለመግባት የሚፈልግ አለመኾኑን ተናግረዋል።

መምሪያ ኀላፊው በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰላም እንዲደፈርስ የሚጥሩ አካላትን በመቆጣጠር ረገድ የሕዝቡ ሚና የላቀ ስለመኾኑም አንስተዋል።

አሁን ላይ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋለው የሰላም እጦት ችግር ዜጎችን የሚያንገላታ መኾኑን በውል በመረዳት እና የዋግን ሕዝብ ሰላም ወዳድነት በተምሳሌትነት በመውሰድ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለስ እንደሚገባም ምልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ማንኛውም ጥያቄ እና ልዩነት ሲኖር በሰላማዊ መንገድ እና በመደማመጥ መቅረብ እና መመለስ አለበት እንጅ ጦርነት ምርጫ ሊኾን አይገባም ነው ያሉት።

ዘጋቢ፡- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በክልሉ እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ እየተሠራ ነው” የአማራ ክልል የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ባለስልጣን
Next article“በዝናብ እጥረት ምክንያት በዚህ የምርት ዘመን ሦስት ቀበሌዎች ምርት አይኖራቸውም” የምሥራቅ በለሳ ወረዳ