ቋሚ ኮሚቴው የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ ዳግም እንዲታይ ወሰነ፡፡

117

ባሕር ዳር፡- ጥር 14/2012ዓ.ም (አብመድ) የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ ዳግም እንዲፈተሽ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ የፍትህና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጠየቀ።

ቋሚ ኮሚቴው የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ትናንት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።
ረቂቅ አዋጁ የክልል መንግሥታት ያሏቸውን ሥልጣንና ተግባራት በማይጋፋ መልኩ እንዲቀራረቡና የጋራ ዕቅድ ነድፈው እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ነው:: በየእርከኑ በመግሥታትና በአቻ ተቋማት መካከል በመርህ ላይ የተመሠረተ ጠንካራ የትብብር ሥርዓት ለመፍጠር እንደሚያግዝም በውይይቱ ተነስቷል፡፡ በረቂቁ ላይ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ መስተዳድሮች እንደ ክልል መጠቀሳቸው ግን አግባብ አለመሆኑን ተወያዮቹ አንስተዋል፡፡

ይህም ረቂቁ ለክልል መንግሥታት የጎንዮሽ ግንኙነት እና የክልልና የፌደራል መንግሥታት የተዋረድ ግንኙነትን እንደሚመለከት ከሚለው ጋር ይጣረሳል ብለዋል። ረቂቁ ክልልና የፌደራል መንግሥትን በእኩል አተያይ የማቅረብ አዝማሚያው ግልጽነት እንደሚጎድለው ያነሱት ተወያዮቹ በረቂቁ ላይ ደንብ የሚያወጣው አካል ተለይቶ አለመቀመጡም የረቂቁን ምልዑነት እንደሚያጎድለው አስረድተዋል።

ረቂቁ ሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ ከተደረገበት በኋላ ይፅደቅ የሚል ሃሳብ ተነስቶ ውይይት እንደተደረገበትም ኢዜአ ዘግቧል፡፡ ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ጋር ሲነጻጸር ኢትዮጵያ ይህን ህግ በማርቀቅ ረገድ መዘግየቷም ነው የተገለጸው፡፡ በረቂቁ መንግሥታት በሚመሰርቷቸው የመድረክ ውሳኔዎች በሦስት አራተኛ ድምፅ ይጽደቅ በሚለው ላይ በማይገኙ የመድረኩ አባላት ላይ ተፈጻሚነትን በተመለከተ የተቀመጠው ሃሳብ ግልጽነት ይጎድለዋል ተብሏል።

ከዚህ ባለፈም ረቂቁ አስገዳጅ መሆን አለመሆኑን በተመለከተ ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት ተደርጓል፡፡ በዚህም ረቂቁ ተሻሽሎ እንዲቀርብ በድጋሜ እንዲታይ ቋሚ ኮሚቴው ወስኗል፡፡

Previous articleከተበዳይ ወገን መሪ ይፈልቃል ብሎ የጠበቀም አልነበረም፡፡
Next articleየደብረ ማርቆስ ነዋሪው ፖሊስ በስህተት የተከፈለውን 100 ሺህ ብር መለሰ።