“በክልሉ እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ እየተሠራ ነው” የአማራ ክልል የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ባለስልጣን

79

ባሕር ዳር: መስከረም 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የትራፊክ አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን እና በሰው እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ እንደሚገኝ የክልሉ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ባለስልጣን ከአሚኮ ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል፡፡

የአማራ ክልል የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ባለስልጣን የመንገድ ትራፊክ ቁጥጥር ዳይሬክተር ደሳለኝ አዳነ እንዳሉት በክልሉ የትራፊክ አደጋ እየጨመረ እንደኾነ ሪፖርቶች ያስረዳሉ፡፡

በተለይም በክልሉ ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ በሚበዛባቸው 5 ሪጅኦፖሊታንት ከተሞች ላይ የትራፊክ አደጋ መጨመሩን ያስረዱት ዳይሬክተሩ 274 ሰዎች ላይ አደጋ መድረሱንም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ከዚህ በፊት ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ የሚበዛባቸው አካባቢዎች ላይ የትራፊክ አደጋ መቀነስ ቢታይም እንደአጠቃላይ ግን አደጋው መጨመሩን ነው የገለጹት፡፡

በተከሰተው የትራፊክ አደጋም ወደ 96 ሚሊዮን 534 ሺህ ብር የሚገመት ንብርት መውደሙን ነው ለአሚኮ የገለጹት፡፡

ለትራፊክ አደጋው መከሰት በዋናነት ከተወሰነው ፍጥነት በላይ ማሽከርከር እና የአሽከርካሪዎች የልምድ ማነስ የሚጠቀስ እንደኾነ ነው አቶ ደሳለኝ ያብራሩት፡፡

እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስም የግንዛቤ ማስጨበጫ ለአሸከርካሪዎች እየተሰጠም ነው፤ ከመንጃ ፍቃድ ጋር በተገናኘ ደረጃውን ጠብቆ እንዲሰጥ ለማድረግ ከማሰልጠኛ ተቋማት ጋር እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም ከተሽከርካሪ ጋር በተገናኘ በዘመናዊ ቴክኖሎጅ ተሽከርካሪዎች እንዲፈተሹ በማድረግ እና የትራንስፖርት ዘርፉን በዘመናዊ ቴክኖሎጅ ተደራጅቶ እንዲሠራ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑ አብራርተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ ኑ ስለ ሀገራችን ሰላምና ፍቅር በአንድነት እንጸልይ” ቆሞስ አባ ለይኩን ወንድይፍራው
Next article“የዋግኽምራ ሕዝብ ሕግና ሥርዓትን አክብሮ የሚያስከብር የሰላም ተምሳሌት ነው” የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ