
ባሕር ዳር: መስከረም 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የግሽን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ ክብረ በዓል መስከረም 21 ይከበራል፡፡ በአራቱም ንፍቅ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንም ከበዓሉ ለመሳተፍ ወደ ግሽን ደብረ ከርቤ ይጓዛሉ፡፡ በርካቶችም ከውጭ ሀገራት ወደ ስፍራው ያቀናሉ፡፡ ሁሉም በአንድነትና በፍቅር በዚያች ሥፍራ ይሰነብታሉ፡፡ በዓሉ በተጠናቀቀም ጊዜ ዓመት ከርመው ይገናኙ ዘንድ ለፈጣሪያቸው አደራ ሰጥተው ወደየመጡበት በናፍቆት ይለያያሉ፡፡
የግሽን ደብረ ከርቤ ዓመታዊ ክብረ በዓል የሚከበርበት ቀን ተቃርቧል፡፡ ለዓመት ቀጠሮ የያዙ ምዕመናንም የቀኑን መድረስ እየተጠባበቁ ነው፡፡
የግሽን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን አሥተዳደሪ ቆሞስ አባ ለይኩን ወንድይፍራው በዓሉን ለማክበር ከነሐሴ 15/2015 ዓ.ም ጀምረው ዝግጅት እያደረጉ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የኮሮና ቫይረስ እና ጦርነት ፈተና ኾኖ እንደቆዬ ያስታወሱት አባ ለይኩን “ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ያሉ ምዕመናን እንደሚመጡ እየገጹልን ነው” ብለዋል፡፡
ምዕመናን መንፈሳዊ አገልግሎቱን በሚገባ እንዲያገኙ ሙሉ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ በግሸን ደብረ ከርቤ ሀገር ሰላም እንድትኾን ከጳጉሜን አንድ ጀምሮ ምሕላ እየተካሄደ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ሀገር ሰላም እንዲኾን እየጸለይን ምዕመናንን ለመቀበል ዝግጁ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
በዓሉን ለማክበር በአካባቢው ከሚንቀሳቀሰው ኮማንድ ፖስት ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የተናገሩት አባ ለይኩን ኮማንድ ፖስቱ በዓሉ ይከበራል እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡ የግሽን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ክብረ በዓል ኢኮኖሚያዊና መንፈሳዊ ጥቅሞች እንዳሉትም ተናግረዋል፡፡ በዓሉ ሲከበር ለሀገር ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡
በግሸን በዓሉን ለማክበር የሚያሰጋ ነገር አለመኖሩን የተናገሩት አባ ለይኩን አማኞች ወደ ሥፍራው መጥተው በረከት እንዲያገኙም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ፈተና በበዛበት ጊዜ ወደ ተቀደሰ ስፍራ መጓዝ ትልቅ ጸጋ እንዳለውም አንስተዋል፡፡ ኑ በኅብረት የልብ ጸሎት አድርገን በሀገራችን የመጣው ፈተና እና መከራ እንዲቀልልን ፈጣሪያችንን እንጠይቅ ነው ያሉት፡፡ በሀገር የሚመጣ ፈተናና መከራ የሚበርደው በጸሎት ነው ያሉት አባ ለይኩን ምዕመናን ወደ ግሽን መጥተው በኅብረት፣ በፍቅር፣ በአንድት እንድንጸልይ እና የሀገራችን ፈተና እንዲወገድ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!