“ኢትዮጵያ ባላት የውኃ ሀብት ከምትጠቀመው ይልቅ ሌሎች የሚጠቀሙት ይበልጣል” አዳነች ያሬድ (ዶ.ር)

55

ባሕር ዳር: መስከረም 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሳቢያ ኢትዮጵያ ባላት ሰፊ የውኃ ሀብት ከምትጠቀመው ይልቅ ሌሎች የሚጠቀሙት ይበልጣል ሲሉ በናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ የናይል ቤዚን ኢንቨስትመንት ፕሮግራም ቀጣናዊ አስተባባሪ ተናግረዋል፡፡ የዓባይ ግድብ ግንባታን በተመለከተ ግብፅ ለመደራደር ፍላጎት ማሳየቷ የሚበረታታ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡

ቀደም ሲል የዓባይ ግድብ የቴክኒክ ቡድን ተደራዳሪ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት በናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ የናይል ቤዚን ኢንቨስትመንት ፕሮግራም ቀጣናዊ አስተባባሪ የኾኑት አዳነች ያሬድ(ዶ.ር) ኢትዮጵያ የውኃ ማማ የሚል ስያሜ ቢኖራትም ከዚህ ሀብት ራሷ ከምትጠቀመው ይልቅ ሌሎች የታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት የሚጠቀሙት ይበልጣል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ የውኃ ማማ መኾኗ አይካድም ፤ ይህ ማለት ግን የተከማቸ ውኃ ወይንም ውኃ የሞላበት ምድር ናት ማለት አይደለም ብለዋል ዶክተር አዳነች፡፡

ከ80 እስከ 90 ከመቶ የሚኾነው የኢትዮጵያ የውኃ ምንጭ በሰሜናዊ ምዕራብ አካባቢ በዓባይ እና ባሮ አካባቢ ባሉ ተፋሰሶች ውስጥ የሚገኝ መኾኑን የጠቆሙት ዶክተር አዳነች፤ በዚህ አካባቢ የሚኖረው የሀገሬው ሕዝብ ብዛት 40 ከመቶ እንደኾነ ጠቁመዋል፡፡

ይሁንና በዚህ ተፋሰስ ያለው ውኃ የገፀ ምድር ውኃ በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ አይቀርም፡፡ ይልቁንም ከታችኛው የተፋሰሱ ሥፍራ የሚገኙ ሀገራት ውኃው በቀጥታ ስለሚደርሳቸው የበለጠ ተጠቃሚ ናቸው ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

በመኾኑም ኢትዮጵያ የውኃ ምንጭና ማማ ናት ማለት ውኃው በሙሉ እኛ ዘንድ ይከማቻል ማለት አይደለም፡፡ በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የምሥራቁ ክፍል ሰፊ ሕዝብ የሚኖርበት እና ከ10 እስከ 20 ከመቶ ብቻ የዝናብ መጠን የምታገኝ ሀገር ናት ብለዋል። ይህ ሰፊ ሕዝብ ውኃ በአግባቡ እያገኘ አይደለም ፤ በመኾኑም አንዳንድ አካላት ኢትዮጵያ ከግድቦች ይልቅ ለምን የከርሰ ምድር ውኃ አትጠቀም ለሚለው ክስ ይህ ምላሽ ነው ብለዋል፡፡

በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሳቢያ ኢትዮጵያ ያላት ሀብት ከምትጠቀመው ይልቅ ሌሎች የሚጠቀሙት ይበልጣል፡፡ ስለዚህ በዚህ አግባብ የውኃ ማማ ናት የሚለውን ሃሳብም መረዳት ይገባል ሲሉ ዶክተር አዳነች አስገንዝበዋል፡፡

በሌላ በኩል ግብጽ በዓባይ ወንዝ ዙሪያ ለመደራደር ፍላጎት ማሳየቷ የሚበረታታ ነው ያሉት ዶክተር አዳነች፤ ድርድር ወይንም ውይይት በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ ችግር የለውም፤ በመርሕ ደረጃም ከውይይት መግባባት ላይ የሚያደርሱ መንገዶች አሉ ብለዋል፡፡

ኢፕድ እንደዘገበው ኢትዮጵያ ቀደም ብሎም ቢሆን በድርድር ታምናለች፤ በዚሁ መንገድም ስትሠራ ቆይታለች፡፡ አሁን ከግብጽ በኩል የታየው ፍላጎትም ችግር የለውም፡፡ ቁምነገሩ ድርድሩ በምን ኹኔታ እና ለምን የሚለው ነው ብለዋል፡፡

በመርሕ ደረጃ ድርድር ማድረጉ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም ያሉት ዶክተር አዳነች፣ ዋናው ነገር እነርሱ ተስማሙ አልተስማሙ ሥራችንን መቀጠል አለብን፣ ነገ መስማማት ይመጣል ብለዋል፡፡

እንደ ዶክተር አዳነች ገለጻ፤ እኛ ያደረግነው ሌሎች ሀገራት ከሚያደርጉት የተለየ አይደለም፡፡ ኾኖም ድርድሩ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስነካ አይደለም፤ የመኾን ዕድልም የለውም፡፡ በዚህ ዙሪያ የእኛ ተደራዳሪዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገው እንደሚሄዱበት ጠቁመዋል፡፡

የሚያስተሳስር ጉዳይ እስካለ ድረስ የሚመለከታቸው አካላት መወያየታቸውን አያቆሙም ያሉት ዶክተር አዳነች፤ በዚህ ረገድ እኛንና የታችኛው የተፋስ ሀገራትን ያቆራኘው የዓባይ ውኃ እስካለ ድረስ መወያየትና መነጋገር አለብን ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰብል ቁጥጥር ሥራ ላይ ትኩረት እንዲደረግ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አሳሰበ፡፡
Next article“ ኑ ስለ ሀገራችን ሰላምና ፍቅር በአንድነት እንጸልይ” ቆሞስ አባ ለይኩን ወንድይፍራው