የሰብል ቁጥጥር ሥራ ላይ ትኩረት እንዲደረግ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አሳሰበ፡፡

39

ባሕርዳር፡ መስከረም 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በ2015/16 የምርት ዘመን ከ5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱ ይታወሳል፡፡ እስከ አሁን የምሥራቅ እና ምዕራብ ጎጃም ዞኖችን የቅርብ መረጃ ሳያካትት የዕቅዱ 94 በመቶ በዘር መሸፈኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር አግደው ሞላ ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡

በምርት ዘመኑ ማሳን በዘር ከመሸፈን ባለፈ ሰብልን ከተባይ፣ ከአረም እና ከበሽታ መከላከል ላይ ትኩረት መደረጉን አንስተዋል፡፡ በተለይም ደግሞ መደበኛ አረምን በባሕላዊ መንገድ እና በኬሚካል የመከላከል ሥራ እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡

በሥራው ላይም፡-
👉 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል
👉 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር መሬት አንደኛ ዙር አረም ታርሟል
👉1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ደግሞ ሁለተኛ ዙር አረም የታረመ ነው
👉ከ336 ሺህ ሊትር በላይ የአረም መከላከያ ኬሚካልም ጥቅም ላይ ውሏል

በ6 ሺህ 450 ሄክታር ማሳ ላይ ቢጫ ዋግ መከሰቱን ያነሱት ዳይሬክተሩ ከ4 ሺህ 500 ሄክታር ማሳ በላይ የመከላከል ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡ 2 ሺህ 500 ሊትር ኬሚካልም ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸዋል፡፡

አንበጣ፣ ተምች እና ግሪሳ ወፍም ስጋት መፍጠራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ አሁን ላይ ግሪሳ ወፍ በምሥራቅ አማራ አንዳንድ አካባቢዎች ታይቷል ብለዋል፡፡

ሊከሰት የሚችልን የተባይ ወረርሽኝ ለመከላከል ደግሞ ከፌደራል መንግሥት ጋር በመቀናጀት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ርጭት ለማከናወን የፌደራል መንግሥት በኮምቦልቻ የእጽዋት ክሊኒክ ኬሚካል ማቅረቡን አንስተዋል፡፡ ይሁን እንጅ በክልሉ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ተባዩ የሚያድርበትን ቦታ ለመለየት እና የተለያዩ ሥራዎችን ተንቀሳቅሶ ለመሥራት መቸገራቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሮች፣ የግብርና ባለሙያዎች እና በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ኀላፊዎች በየጊዜው የሰብል ቁጥጥር ሥራ እንዲሠሩም አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ፍትሐዊ ውክልና እንዲኖር ጥሪ አቀረቡ።
Next article“ኢትዮጵያ ባላት የውኃ ሀብት ከምትጠቀመው ይልቅ ሌሎች የሚጠቀሙት ይበልጣል” አዳነች ያሬድ (ዶ.ር)