ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ፍትሐዊ ውክልና እንዲኖር ጥሪ አቀረቡ።

45

ባሕርዳር፡ መስከረም 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ፍትሐዊና አካታች መሆን እንደሚገባው አስታወቁ።
78ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በኒውዮርክ እየተካሄደ ይገኛል።

የጀርመን መራሔ መንግስት ኦላፍ ሹልዝ ከጉባኤው ጎን ለጎን የተመድ እና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ማሻሻያ አስመልክቶ ያዘጋጁት መደበኛ ያልሆነ የምክክር ስብስባ ተካሄዷል።

በስብስባው ላይ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ የአፍሪካ አባል አገራትና ሌሎች አገራት ተሳትፈዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ ጉዳይ ለረጅም ጊዜ የቆየ ጥያቄ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በማሻሻያው ላይ ከአፍሪካ ጋር የጋራ አቋም እንዳላት ጠቅሰው ምክር ቤቱ ፍትሐዊና አሳታፊ እንዲሆን የዓለም ሁሉ ፍላጎት ነው ብለዋል።

ነገሮችን ባሉበት የማስቀጠል አቋም ውስጥ ያለው ምላሽ ያለመስጠት ፍላጎት የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የልማት ፋይናንስ ፍላጎት እንዳያሟሉ ማድረጉን አመልክተዋል።

የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት አስቸኳይ ማሻሻያ በማድረግ አስፈላጊውን የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ነው አቶ ደመቀ ጥሪ ያቀረቡት።

የጀርመን መራሔ መንግስት ኦላፍ ሹልዝ በቅርቡ በኢትዮጵያ ባደረጉት የስራ ጉብኝት ያሳዩትን አጋርነትና ወዳጅነት አድንቀዋል።

በስብስባው ላይ የተገኙት የኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ሞሪሺየስና ኮሞሮስ ፕሬዝዳንቶች የፀጥታ ምክር ቤት ተቋማዊ ማሸሻያ እንደሚያስፈልገው በመግለጽ የየአገራቸውን አቋም አንጸባርቀዋል።

አቶ ደመቀ በስብስባው ጎን ለጎን ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት እና ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ሚርጃና ኤገር ጋር ፍሬያማ ውይይቶችን ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት ተጓዦች ለእንግልት እየተዳረጉ ነው” የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ባለስልጣን
Next articleየሰብል ቁጥጥር ሥራ ላይ ትኩረት እንዲደረግ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አሳሰበ፡፡