“በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት ተጓዦች ለእንግልት እየተዳረጉ ነው” የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ባለስልጣን

47

ባሕርዳር፡ መስከረም 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በተከሰተው የሰላም እጦት ምክንያት ሕዝቡ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮቹን ፈጽሞ ለመመለስ አስቸጋሪ ሁኔታ እንደተፈጠረበት የክልሉ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ባለሥልጣን ገልጿል፡፡

በክልሉ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ባለሥልጣን የመንገድ ትራፊክ ቁጥጥር ዳይሬክተር ደሳለኝ አዳነ በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች የሚስተዋለው የትራንስፖርት አገልግሎት የታሪፍ ጭማሪ ሕዝን ለአላስፈላጊ ወጭ እና እንግልት እየተዳረገ ስለመኾኑም አስረድተዋል፡፡

ሰላም ለትራንስፖርት ዘርፉ ወሳኝ መኾኑን ያስገነዘቡት ዳይሬክተሩ አሁን ላይ የትራንስፖርት ስምሪት ባለባቸው አካባቢዎች የተሻለ አገልግሎት እየተሰጠ ስለመኾኑም አንስተዋል፡፡

በተለይም አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው የወሎ እና ጎንደር መስመሮች ላይ የትራንስፖርት ስምሪቱ በሚገባ እየተሰጠ ተጓዦች ለእንግልት እንዳይዳረጉ ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑም አብራርተዋል፡፡

የፀጥታ ችግሮች ባሉባቸው የገጠር አካባቢዎች እና አንዳንድ ዋና ዋና መስመሮች ላይ የኅብረተሰቡን እንግልት ለመቀነስ አለመቻሉን ጠቁመዋል፡፡

ማኅበረሰቡ ጉዳዩን ለመፈጸም ሲወጣ ከሚጨመርበት ታሪፍ በተጨማሪ ከማይፈልገው ቦታ ላይ እንዲወርድ እየተደረገ ለእንግልት እና ለተጨማሪ ወጭ እየተዳረገ ነው ብለዋል፡፡

ለወትሮውም ቢኾን በቁጥጥር ውስጥም እንኳን ኾኖ አስቸጋሪ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት አሁን ላይ ኅብረተሰቡን ለበለጠ ምሬት ዳርጎታል ነው ያሉት፡፡

ሰላምን በማስጠበቅ በኩል ከፍተኛውን ድርሻ መንግሥት ቢወስድም ኅብረተሰቡም ለሰላም ዘብ በመቆም ያለውን እንግልት እና የሚደርሰውን ኪሳራ እንዲያስቀር ትብብር ሊያደርግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየግብርናው ዘርፍ በዋና ዋና ተግባራት ከዕቅድ በላይ ዕድገት ማስመዝገቡን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።
Next articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ፍትሐዊ ውክልና እንዲኖር ጥሪ አቀረቡ።