
ባሕርዳር፡ መስከረም 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የግብርና ዘርፍ በአስር ዓመቱ የልማት ዕቅድ የመጀመሪያዎቹ 3 ዓመታት (2013-2015) በዋና ዋና ተግባራት ከዕቅድ በላይ ዕድገት ማስመዝገቡን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል።
የአስር ዓመት ዕቅድ የመጀመሪያዎቹ 3 ዓመታት (2013-2015) ዋና ዋና አፈጻጸሞች የግብርናው ዘርፍ ከዕቅድ በላይ ዕድገት ማስመዝገቡን ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር የወጣው ሪፖርት ያመለክታል፡፡ በሪፖርቱ የግብርና ዘርፍ ዕድገት በ2013 ከነበረበት 5.1 በመቶ በ2014 ወደ 5.8 በመቶ ያደገ ሲሆን በ2015 ደግሞ 6̄.3 በመቶ እድገት አስመዝግቧል፡፡
ዘርፉ በስሩ ካሉት ንዑስ ዘርፎች መካከል ግብርናውን ለማሳደግ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የሰብል ምርት ሲሆን ለዘርፉ ማደግ 65.5 በመቶ አስተዋፆ አበርክቷል፡፡ ደን 8.6 በመቶ እና እንሰሳት 25.9 በመቶ ድርሻ ነበራቸተው።
በ2015 ዓ.ም ጠቅላላ የሰብል ምርት 627 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ታቅዶ 639 ሚሊየን ኩንታል ምርት ማግኘት ተችሏል፡፡ በዘር የተሸፈነ መሬትን በተመለከተ የአነስተኛ አርሶ አደሮች በመኸር በአዝርዕት የተሸፈነ መሬት በ2012 ከነበረበት 13 ሚሊየን ሄክታር በ2015 ወደ 14.06 ሚሊየን ሄክታር ያደገ ሲሆን ይሄም በትላልቅ ኢንቨስትመንት በአዝርዕት ሰብል የተሸፈነ መሬት ብዙ ለውጥ ባላማምጣቱ ምክንያት ምርትና ምርታማነት ለጨመረው በዋናነት መሬትን ከማስፋት ይልቅ ምርታማነት ላይ ትኩረት በመደረጉ ነው።
በመስኖ የስንዴ ምርትን ከ2013 ከነበረበት 0.6 ሚሊየን ኩንታል በ2015 ወደ 47 ሚሊዮን ኩንታል ማሳደግ ተችሏል ።
በግብርና ዘርፍ በእንስሳት ምርት አፈጻጸም ባለፍት 2 አመታት የእንስሳት ልማት ንዑስ ዘርፍ በአማካይ በ8.4% ያደገ ሲሆን ከ10 ዓመቱ ዕቅድ አንፃር በ0.8 በመቶ ብልጫ አለው።
የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት በ2015 ዓ.ም 12.9 በመቶ ታቅዶ 10.8 በመቶ የቀረበ ሲሆን ለዚህም የፀጥታ ችግር እንደ አንድ መሰናክል በመሆኑ ከታቀደው በታች የሆነ አፈፃፀም ሊታይ ችሏል፡፡
የመኸር ወቅት በአነስተኛ አርሶ አደሮች የአዝርዕት ምርት እና በአነስተኛ አርሶ አደሮች እና በሰፋፊ እርሻ በመስኖ የተመሰረተ አዝርት ፣የአትክልት ፣ፍራፍሬና ስራስር ምርት ከፍተኛ የዕድገት ሽግግር የታየባቸው ዘርፎች ናቸው፡፡
የግብርናው ዘርፍ ምርቱን ለገበያ ለማቅረብ ሌላው ቁልፍ ገጽታ የምርቶቹን ትክክለኛ ዋጋ የማግኘት ችግርን ከመፍታት ባለፈ ለዋጋ መረጋጋት ትልቅ ሚና ይጫወታል። ከዚህ አንፃር በእቅድ ዘመኑ ታሳቢ የተደረገ የግብርና ምርቶች የገበያ ትስስር ለመፍጠር በጊዜው ለ35 ሚሊዮን ኩንታል እህል የገበያ እድል ለመፍጠር ታቅዶ የነበረ ሲሆን አፈጻጸሙም 24.4 ሚሊዮን ኩንታል (70 በመቶ) ነው። በተመሳሳይ 14 ሚሊዮን ኩንታል የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ለገበያ ለማቅረብ ታቅዶ 9.6 ሚሊዮን ኩንታል (የእቅዱ 68 በመቶ) ለማቅረብ ተችሏል።
በአረንጓዴ አሻራ ፥ በሌማት ትሩፋት ፥ በከተማ ግብርናና በአትክልትና ፍራፍሬም ከፍተኛ ለአለም ተሞክሮ የሚሆኑ አፈጻጸሞች መመዝገባቸዉን ተነተነዉ ሪፖርቱ ይህም በቀጣይ የመካከለኛ ዘመን ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሚሆን ተመላክቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!