
ባሕር ዳር: መስከረም 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሁሉም ተማሪዎች በወቅቱ እንዲመዘገቡና ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ትምህርት ቢሮ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በአማራ ክልል ከነሐሴ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የተማሪዎች ምዝገባ እየተካሄደ ነው፡፡ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነትና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጌታቸው ቢያዝን የተማሪዎች ምዝገባ ከሌሎች ዓመታት አንጻር ሲታይ የተጓተተ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡ በአማራ ክልል በተፈጠረው ችግር ምክንያት ምዝገባው በተፈለገው ልክ አለመሄዱንም ገልጸዋል፡፡ ከአሁን በፊትም የተማሪዎችን መመዝገቢያ ቀናት መራዘም ይገጥም እንደነበር ያስታወሱት ኀላፊው የዘንድሮው ግን ከሌሎች ዓመታት አንጻር ሲታይ መጓተት ይስታዋልበታል ነው ያሉት፡፡
በአማራ ክልል ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ እቅድ ተይዞ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ እስካሁን 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተማሪዎች ተመዝግበዋል ነው ያሉት፡፡ ከባለፉት ዓመታት የምዝገባ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የዘንድሮው ዝቅተኛ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ከነሐሴ 23 እስከ ጳጉሜን 3 ቀን 2015 ዓ.ም ተማሪዎችን ለመመዝገብ አቅደው እንደነበር ያስታወሱት ኀላፊው ምዝገባው በተፈገው ልክ ባለመኾኑ እስከ መስከረም 11 ቀን 2016 ዓ.ም መራዘሙን ገልጸዋል፡፡ ያለውን ወቅታዊ ኹኔታ ታሳቢ በማድረግ የምዝገባ ቀኑ ለተጨማሪ ቀናት የሚራዘምበት እድል እንደሚኖርም ተናግረዋል፡፡ የጸጥታ ችግር በሌለባቸው አካባቢዎች ምዝገባው መቀጠሉንም ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ያሉ ትላልቅ ከተሞች አፈጻጸማቸው የተሻለ መኾኑን እና እስከ መስከረም 11 ቀን 2016 ዓ.ም የሚጨርሱበት እድል እንደሚኖርም ተናግረዋል፡፡
ዞኖች እና ከተማ አሥተዳደሮች የተማሪዎችን ምዝገባ አጠናክረው እንዲቀጥሉ እየሠሩ መኾናቸውንም አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡ ትምህርት ቤት ትውልድ የሚቀረጽበት መኾኑን የተናገሩት ኀላፊው ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት መላክ ግድ እንደሚልም አንስተዋል፡፡ የተማሪዎችን ምዝገባ በወቅቱ ማጠናቀቅ እና በተያዘው ጊዜ ማስተማር ካልተቻለ የክልሉ ተማሪዎች ተወዳዳሪነት ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ኮሮና ቫይረስ እና ጦርነት የክልሉን የትምህርት ሥራ በእጅጉ ጎድቶት እንደቆየ የተናገሩት ኀላፊው አሁን ያለው የሰላም እጦትም ተጨማሪ ጫና ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡ ትምህርት በየትኛውም ኹኔታ መቋረጥ እንደማይገባውም ተናግረዋል፡፡ ብቁና ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለመፍጠር ተማሪዎች እንዲመዘገቡና ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይገባዋል ሲሉም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በአጭር ጊዜ ተማሪዎች እንዲመዘገቡና መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራው መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም እንዲጀመር ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የሚቀጥለው ትውልድ የተሻለ እንዲኾን ዛሬን በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አቶ ጌታቸው አመላክተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!