
ባሕር ዳር፡- ጥር 14/2012ዓ.ም (አብመድ) 7ኛው የመላው ሰሜን ጎንደር ወረዳ አቀፍ የባህልና ዘመናዊ ስፖርቶች ውድድር በደባርቅ ወረዳ አሸናፊነት ተጠናቅቋል ።
ውድድሩ ለተከታታይ ዘጠኝ ቀናት በ16 የስፖርት አይነቶች ነው የተካሄደው። በባህልና ዘመናዊ ስፖርቶች ውድድሩ ደባርቅ ወረዳ አሸናፊ ሆኗል። ዳባት ወረዳና ደባርቅ ከተማ አስተዳደር ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቅቀዋል። በየዳ ወረዳ ደግሞ በስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማት ተበርክቶለታል።
ውድድር ዞኑን የሚወክሉ ለዘመናዊና ባህላዊ ስፖርቶች ተወወዳዳሪዎችን ለመምረጥ እንዳስቻላቸው የሰሜን ጎንደር ዞን ስፖርት ቡድን መሪ አቶ አዬልኝ ካሳ ተናግረዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወርቁ ለምለሙ ጨዋታው ያለምንም የጸጥታ ችግር መጠናቀቁ ስፖርት ወንድማማችነትን አንድነትንና ሰላምን ማጠናከሪያ ስለመሆኑ ማሳያ እንደሆነ ነው የተናገሩት።
ሰሜን ጎንደር ዞን በአትሌቲክስ ዘርፉ የሚታወቅ አካባቢ በመሆኑ ጠንክሮ በመሥራት ውጤታማ ተወዳዳሪዎችን ማፍራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዉድድሩ ባሳለፍነው ሳምንት ሲጀመር የዳባት አትሌቲክስ መንደር ግንባታ የመሠረት ድንጋይ መቀመጡ ይታወሳል። የደባርቅ ወረዳ አስተዳድር ለአትለቲክስ መንደሩ ግንባታ 3 ሚሊዬን ብር ድጋፍ በማድረግ የግንባታ ወጪውን ሲሸፍን የደባርቅ ከተማ አስተዳደር ደግሞ ለአትሌቲክስ መንደሩ ግባታ የሚሆን መሬት ሰተዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ደስታ ካሳ- ከዳባት