“እየሠራን ሥንደራደር አትራፊ እንኾናለን”

35

ባሕርዳር፡ መስከረም 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዓባይን መገደብ እና ለኢትዮጵያ ጥቅም ላይ መዋል ረጅም ዘመን የቆየ ሃሳብ ነበር፡፡ ሃሳብን ወደ ተግባር ለመቆየር ግን ዘመን እና የታደለ ትውልድ ያስፈልጋል፡፡ መልካም አስበው፣ ሩቅ አልመው በቅርብ በበርካታ ምክንያቶች ከቅርብ የቀሩ አሉና፡፡

ዓባይን ለኢትዮጵያ ጥቅም የማዋል ሃሳብ ዘመንና እድለኛ ትውልድን ሲጠብቅ ኖሮ ሃሳብ እውን ኾኗል፡፡ ዓባይም መገደብ ከተጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ዓባይን ለመገደብ ሃሳብ ከተጠነሰሰበት ዘመን ጀምሮ አሁን ግድቡ እስካለበት ጊዜ ድረስ ፈተናዎች በርክተዋል፣ ጫናዎችም አይለዋል፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ግን ፈተናዎቹን በአንድነታቸው እና በብልሃታቸው እየመከቱ የዘመናት ሃሳባቸውን እውን አድርገዋል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት በአዲስ ዓመት ዋዜማ መበሰሩ ይታወሳል፡፡ አራተኛው የውኃ ሙሌት ለኢትዮጵያውያን የአዲስ ዓመት ሥጦታ ኾኖ የተበረከተ ነው፡፡ ለረጅም ዓመታት በሃሳበቸው፣ በጉልበታቸው እና በእውቀታቸው ለተረባረቡለት ኢትዮጵያውያን ደስታን ፈጥሯል፡፡

በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የብሉ ናይል የውኃ ምርምር ተቋም ተመራማሪ እና የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር አበበ ይርጋ የዓባይ ውኃ ሙሌት የአንድ ሀገር ብቻ ይመስል የነበረውን ወንዝ የጋራ እንደኾነ ያሳየ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ግብጽ ዲፕሎማሲያዊ ያልኾኑ እና ዓባይን ለራስ ብቻ የማድረግ አቋሟን የማስቀየር አቅም እንዳለውም አንስተዋል፡፡ እየሠራን ሥንደራደር አትራፊ እንኾናለን፣ ተደራድሮ መሥራት እንደማይቻል ያለፉት ታሪኮች ያሳያሉ፣ ከሠሩ በኋላ መደራደርም አይቻልም፤ የኢትዮጵያ መርህ እየሠሩ መደራደር መኾን አለበት ነው ያሉት፡፡

ሱዳንን ከውኃ አቅርቦት ባለፈ የግድቡ ጥራት እንደሚያሳስባት የተናገሩት ተመራማሪው የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለሱዳን ስጋት እንደማይኾንም ገልጸዋል፡፡ የግድቡ መረጃ ሌላኛው ሱዳን የምትፈልገው እና የሚያሳስባት መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ሀገርን አላስፈላጊ ጫና ውስጥ የሚከቱ የድርድር አካሄዶች እንዳይኖሩ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከሌሎች የዓለም ግድቦች በተለየ መልኩ ጫና የሚደርስበት ስለመኾኑ ሲናገሩ ግድቡ የኢትዮጵያን አቅም የሚጨምር መኾኑ፣ ሌሎች ግድቦችን እንድንገድብ በር ይከፍታል፣ የግብጾች አላስፈላጊ ቁጥጥር እና የበላይነት ይክስማል፣ ይህ እንዳይኾን ኢትዮጵያ ላይ ጫና መብዛቱን ነው ያነሱት፡፡

ግብጽ የሕዳሴ ግድብ የደኅንነት ጉዳይ ኾኖ እንዲታይ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት እንደወሰደችው ያስታወሱት ተመራማሪው ይሄንንም ግብጽ ኢፍትሃዊ የኾነ ጥቅሟን ለማስከበር የሄደችበትን ርቀት እንደሚያሳይም አመላክተዋል፡፡ በዓለም ላይ በርካታ ግድቦች ተገንብተዋል፣ ችግሮችም ተፈጥረዋል፣ በዓባይ ልክ ችግሩ የገዘፈበትና ችግሩን ባልተለመደ መልኩ እንዲፈታ የተሞከረበት አለመኖሩንም አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ ላይ የወሰደችው አቋም ወደፊት ለሚኖሩ ግድቦች በር ከፋች መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የዓባይ ግድብ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጥረው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ላቅ ያለ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ ሀገረ መንግሥት ግንባታ እና ዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነት ላይ ከፍ ያለ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ እንድታድግና ተሰሚነቷ ከፍ እንዳይል የሚፈልጉ ሀገራት ተጽዕኗቸው ከፍ ያለ መኾኑን ያነሱት ተመራማሪው አሁን አሁን ኢትዮጵያውያን ለጠላት የሚመቹ እየኾኑ መምጠታቸውን ነው የገለጹት፡፡ በኢትዮጵያ የሚፈጠሩ ችግሮች ሁሉንም ውጫዊ ከማድረግ ይልቅ በውስጥ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

የራሳችንን ችግር እየፈታን ውስጣችንን ካስተካከልን የውጭ ኀይሎች እጃቸውን ማስገባት አይቻላቸውም ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድቡ ለአፍሪካ ከባቢ አየር ነጻ የኾነ ኀይል የማቅረብ አቅም እንደሚፈጥርላትም ገልጸዋል፡፡ ከነዳጅ በላይ ውኃ ውድ ሃብት መኾኑን ያነሱት ተመራማሪው ከዝናብ ጥገኛ የኾነውን የኢትዮጵያ ግብርናን እንደሚያዘምነውም ተናግረዋል፡፡ በዝናብ ብቻ የተመሠረተውን ግብርና አማራጭ ይዞ ይመጣልና፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ የበይ ተመልካችነቷ አብቅቶ የውኃን ጥቅም የተረዳች፣ በራሷ አቅም የገነባች ፣በዓለም አቀፍ መርኾዎች አማካኝነት ጥቅሟን የምታስከብር ሀገር መኾኗን የምታሳይበት መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ ለጎረቤት ሀገራትም ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚሰጥ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረትን የ2063 አጀንዳን እውን ለማድረግ የሕዳሴ ግድብ ታላቅ አስተዋጽዖ እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የቀጣናው ኀያል እንድትኾን እንደሚያደርጋትም ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሃብቷና ተሰሚነቷ ከፍ እንዲል ሰላምና የሕግ የበላይነት ሊኖሩ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ ጦርነት ውስጥ ኾኖ ማልማትና የሕዝብ ድጋፍ ማግኘት እንደማይቻልም ገልጸዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በሚገባው ልክ ውኃ መያዝ እንደሚገባውም አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቀጣይ ለሚኖራት የሕዳሴ ግድብ ሥራዎች እና ድርድሮች የሚፈጠሩትን ጫናዎች ለመቋቋም መዘጋጀት እንደሚገባትም አመላክተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት ማሻሻያ ያስፈልገዋል” አቶ ደመቀ መኮንን
Next article“በተፈጠረው የሰላም እጦት ክልሉ ከፍተኛ ገቢ እያጣ ነው” የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ