
ባሕርዳር፡ መስከረም 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ብልኾች በነገው ተስፋ የዛሬን መከራ ይረሳሉ፤ የዛሬውን የመከራ ማዕበልም በነገ ተስፋ ይሻገራሉ፡፡ ነገን ተስፋ የሚያደርጉ ሁሉ ዛሬን በጽናት ይቆማሉ፡፡ ነገን ተስፋ የሚደርጉ ሁሉ የዛሬን መከራ በጥበብ እና በጠባቡ ሁሉ ያልፋሉ፡፡ ስለነገ ተስፋ ያላቸው የዛሬው ጨለማ እና መሰናክል ሁሉ ከተራ ፈተናነት አያልፍም፡፡
ተስፋ መከራን ታሻግራለች፤ ክፉ ዘመንን ታሳልፋለች፡፡ ተስፋ የሚያደርጉ ሁሉ ከሰው፣ ከፈጣሪ እና ከተፈጥሮ ጋር ሁሉ ስምሙ ናቸው፡፡ ተስፋ የሚያደርጉ እና ስለነገ ተስፋ ያላቸው ሁሉ ውስጣዊ ሰላም አላቸው፡፡ የሰው ልጅ የስብእና መሰረቱ እና የሞራል ልህቀቱ ምክንያት ውስጣዊ ሰላም ማግኘቱ ነው ይባላል፡፡ በምድር ላይ ተስፋ ከማጣት የከፋ የሰው ልጅ መከራ የለም ይላሉ ሊቃውንት፡፡ ሰውን የሚያኖረው የትናንት ትዝታ ብቻ ሳይሆን የነገ ተስፋም ጭምር ነው የሚሉት አበው ተስፋ ማጣት ከሞትም ትበልጣለች ይላሉ፡፡ ሸክላ ቅርፁ በሰሪው እጅ እንደሚወሰን ሁሉ ፍጡርም በፈጣሪው ተስፋን ያደርጋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን የመከራን ማለቅ፤ የእዳን መለቃለቅ ተስፋ አድርገው ከሚጠብቁባቸው ምክንያቶች አንዱ የአዲስ ዓመት መምጣት ነው፡፡
አነሆ በኢትዮጵያ ምድር ሁሉ አሮጌው ዘመን ወጥቶ፤ አዲሱ ዘመን ተተክቶ መስከረም በአዲስ ዘመን ዙፋን ላይ ተሰይሟል፡፡ ኢትዮጵያውያን ጭጋግ የበዛበትን፣ የመብረቅ ንውጽውጽታ ያየለበትን፣ ማዕበል የሚደነፋበትን፣ በተራራዎች ላይ ጉም የሚጎተትበትን፣ ሰማዩ በደመና የሚከለልበትን የክረምት ጭፍና ወራት አሳልፈው አዲስ ዘመን ብስራት ላይ ደርሰዋል፡፡
አዲሱን ዘመን በጠባ ጊዜ ቢጫ የአደይ አበቦችን ይዘው እንቁጣጣሽ የሚሉት ኢትዮጵያዊያን ልክ እንደዘመን መፈራረቅ መከራውን በደስታ፤ መከፋቱንም በፌሽታ የመለወጥን ጥበብ ተክነዋል፡፡ ችግሮቻቸውን ሁሉ ከአሮጌው ዘመን ጋር አራግፈው በአዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ ይሰንቃሉ፤ ይኽ የኢትዮጵያዊያን የተለየ መሰጠት ነው የሚሉም አይታጡም፡፡
መከራን በመካሪነቱ እና ፈተናን በአስተማሪነቱ ተስፋ አድርገው የሚቀበሉት ኢትዮጵያዊያን መከራና ስቃዩ፣ ሞትና መፈናቀሉ፣ ረሃብና ቸነፈሩ ሁሉ ከአሮጌው ዘመን ጋር ያልፍ ዘንድ ተስፋን ያደርጋሉ፡፡ ሰላምና ፍቅር፤ ተድላና ደስታ ከአዲሱ ዘመን ጋር በጉጉት ይጠበቃሉ፤ ስለ ምን ካሉ አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋን ይዞ እንደሚመጣ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ በብርቱ ይታመናልና፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአራቱ ጉባኤያት መምህር እና በጎንደር የመንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አስተዳደሪ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ “ተስፋን” ሲገልጹት አለኝ፣ ይቆየኛል፣ ይደረግልኛል፣ ለእኔ ይህ ነገር ተዘጋጅቶልኛል፣ ለእኔም ይጠቅመኛል፣ ለክብርም ይሆነኛል ተብሎ የሚታሰብ ነገር ሁሉ ነው ይላሉ፡፡
ከፍጥረት ተቀዳሚው አዳም የተወረሰ የቀጠሮ ተስፋ አለ የሚሉት ሊቁ ይህ ይሆንልሃል፣ ትሾማለህ፣ ትሸለማለህ፣ ትማራለህ፣ ትመረቃለህ፣ ባለጸጋም ትሆናለህ ሁሉ የቀጠሮ ተስፋዎች ናቸው ይላሉ፡፡ የሰው ልጅ የህሊና ተስፋም አለው ሰርቶ መለወጥ፤ አፍርቶ ማጌጥ የህሊና ተስፋዎች ናቸው፡፡ አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋን ይዞ ይመጣል፤ ያለፈው ዘመን የያዘውን ግሳንግስ ሁሉ ጨርሷል፤ ለሚመጣው አዲስ ዓመትም አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ በአዲስ ዓመት የክረምቱ ጭጋግ ይገለጣል፣ በደመና የተሸበበው ሰማይ ይጠራል፣ ብርዱና ጭጋጉ ሙቀትና ድምቀት ባላት ፀሐይ ይተካል፣ የውሽንፍሩና የጎርፉ ወራት አልፎ የሰከነ አየር የጠራ ውኃ ይስተዋላል፡፡ በኢትዮጵያ የዘመን ኑባሬ ሂደት ውስጥ የሚስተዋሉት ክስተቶች ሁሉ ለሰው ልጅ ተስፋ ትምህርት ሆነው ይቀርባሉ ይላሉ ሊቁ ፍጡርን ከተፈጥሮ ጋር ሲያዋድዱ፡፡
አዲስ ዓመት በክረምት የተሸፈነውን ተስፋ ይገልጣል፡፡ ምድርም የያዘችውን እና የተጣለባትን ተስፋ በዘመን ቀመር ሳታዛባ ትገልጣለች፡፡ ከነጎድጓዱ እና ዶፍ ዝናቡ በኋላ፤ ከማዕበሉና ከጎርፉም ቀጥሎ አዲሱ ዓመት ሲመጣ ምድር በአበባ ትዋባለች፣ ፍሬም ትሰጣለች፣ ሰውም ዘሩ ፍሬ ያፈራልኛል፣ እሸትም ያሳየኛል እያለ ተስፋ ያደረገውን ያገኛል፡፡ የተራበው ሁሉ እሸት አግኝቶ ይቀምሳል፣ ረሃቡንም ያስታግሳል ይላሉ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ተስፋን ከተፈጥሮ ዑደት ጋር አዋደው ሲያመሰጥሩት፡፡
ህጻናት በአዲስ ዓመት ብስራት ማለዳ አበቦችን ታቅፈው በየበራፎቻችን ሲደርሱ ተስፋችን እውን ስለመሆኑ የምናስታውስ ግን ስንቶቻችን እንሆን? ገበሬ ለምርቱ፣ ዳኛ ለችሎቱ፣ ተማሪ ለእውቀቱ፣ ሹመኛ ለሹመቱ፣ ካህን ለጸሎቱ አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ እና እድል ሰጣቸው ይባላል ይሉናል፡፡ ተማሪዎች በአዲስ ዓመት አዲስ እውቀት ለማየት ተስፋን ያደርጋሉ፡፡ ነጋዴ ነግዶ፣ የታሰረው ተፈትቶ፣ ህሙማን ተፈውሰው ያዩ ዘንድ ተስፋቸው የአዲሱ ዘመን መምጣት ነው የሚሉት ሊቁ ሰላም ግን የሰው ልጅ በአዲስ ዓመት ተስፋ ያደረገበትን ነገር ሁሉ እውን እንዲሆን ቁልፏ ነች ይላሉ፡፡ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ የአዲስ ዓመት ተስፋ እውን ይሆን ዘንድ መሠረቱ ሰላምና ፍቅር ነውም ይላሉ፡፡
ምንም እንኳን ሁሉም የፍቅርና የሰላም ዘመን ይሆንለት ዘንድ ቢመኝም በሽታ የሚመጣበት ዘመን አለው፤ ጦርነትም የሚያጋጥምበት ዘመን አለው፤ የሚሉት ሊቁ ተስፋ ለምናደርግ ለእኛ ለሰው ልጆች ግን ሁሉም አልፎ ሰላም የሚሆንበት ዘመን ይመጣል ይላሉ፡፡ ፈጣሪ ለሁሉም ነገር ዘመንን ሰጥቶታል፤ ሁሉንም በዘመን ወስኖታል፤ ያም ይሆን ዘንድ ግድ ነው ብለውናል፡፡ በዘመን የሚመጣውን ተስፋ እና በረከት የሚቀበሉ ባለተስፋና ቅን አሳቢ ትውልድ ግን ያስፈልጋሉ ነው ያሉት፡፡
በዘመን ባቡር ውስጥ መከራው አልፎ እና ጦርነቱ ተላልፎ ዘመን ለፍስሀ ጊዜ ለንስሃ እንደሚገኝ ግን እንኳን ሰው እንስሳትም ተስፋ ያደርጋሉ ነው ያሉት፡፡ በቸርነቱ የፍቅርና የሰላም ዘመን እንዲመጣ፣ አዲሱ ዘመን ጦርነት የሌለበት፣ ሰላም ያየለበት፣ ፍቅር የነገሠበት፣ ትዕግስት እንደ እዮብ ለሰው ሁሉ የሚሰጥበት፣ የተጣላው የሚታረቅበት፣ የበለደው ክሶ፣ የቀማ መልሶ፣ የተበደለም ተክሶ፣ ሁሉም አንድ ሆኖ ይኖር ዘንድ ተስፋ ይደረግበታል፡፡ ሰው ሁሉ በአዲስ ዓመት ሁሉ ነገር ይስተካላል እያለ በተስፋ ይጠብቃል፡፡
ክረምት እና እንቅልፍ የሞት ምሳሌዎች ናቸው የሚሉት ሊቁ ክረምት የቅጠል ዘመን ነው፤ ፍሬ አይገኝበትም፡፡ “ስደታችሁ በክረምትና በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ” እንደተባለ ክረምት ላዩም ታቹም ውኃ ነው፤ የቅጠል ዘመን ነው፣ እናንተም ፍሬ ሳታፈሩ፣ መልካም ነገር ሳታገኙ፣ በሞት እንዳትጠሩ ስለኢትዮጵያ ሰላም ምከሩ ነው ያሉት፡፡
ክረምት በአዲሱ ዓመት እንደሚቀየር ሁሉ የሰው ልጅ ልቦና ጦርነት እንዲቀር መስማማትን፣ መመካከርን፣ ለሀገርና ለሕዝብ ማሰብን ማስቀደም አለበት፡፡ የበላይም የሆነ የበታች፣ መሪም ሆነ ተመሪ ለሀገር ካሰበ ግጭት በስምምነት፤ ጦርነት በውይይት ይቀለበሳል ይላሉ፡፡ ለሀገር ማሰብ እና ማስታዋል ከጎደለ ግን ሁሉም ነገር የግጭት አውድማ ከመሆን አይድንም፡፡ እናም ሁሉም ማስታዋልን ገንዘቡ ሊያደርግ ይገባል ይላሉ፡፡
የሰው ልጅ አስተሳሰብ እንደ ዘመን ሁሉ መለወጥን ይሻል የሚሉት ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ የሰው ልጅ አስተሳሰብ እስካልተለወጠ ድረስ የዘመኑ መለወጥ ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ ክቡር የሆነው ፍጡር ለምን ይሞታል? ሃብትና ንብረትስ ስለምን ይውድማል? የሚለውን በውይይት መፍታት ይበጃል፡፡ በፉክክር ዘመኑን መዋጀት፤ መጻዒውን ጊዜ ማበጀት አይቻልም የሚሉት ሊቁ አዲሱ ዘመን ስለመጣ ብቻ የሚለውጠው ነገር አይኖረውም፤ ይልቁንም ልክ እንደ ዘመን የሰው ልጅ እሳቤም መለወጥ ይኖርበታል፡፡ አስተውሉ፣ ተስፋን አድርጉ፣ በተስፋም ተመላለሱ፣ ምድር ፍሬን እንድትሰጥ፣ ፍጥረታትም ከፍሬዋ እንዲመገቡ፣ ክፉ ዘመን ሁሉ እንዲርቅና እንዲጠፋም መልካም አድርጉ፤ በተስፋም ተሸጋገሩ ሲሉ ሊቀ ሊቃውንቱ መልካም ምኞታቸውን አካፍለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!