“ዓባይ የኢትዮጵያን እውነት ገልጧል”

55

ባሕር ዳር: መስከረም 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዓባይ ወንዝ ብቻ አይደለም ውኃ ብቻ የሚፈስስበት፣ ዓባይ ስም ብቻ አይደለም አንድ ወንዝ የሚጠራበት፣ ዓባይ መዝገብ ነው የሀገር ታሪክ የሚነበብበት፣ ዓባይ ብዕር ነው የዘመን ታሪክ የሚጻፍበት፣ ዓባይ ማንነት ነው ታላቅ ሀገር፣ ታላቅ ሕዝብ የሚገለጥበት፣ ዓባይ ጥበብ ነው ሕዝብ ሁሉ ከጥበቡ የሚቀዳበት፣ ዓባይ ዜማ ነው ሊቃውንቱ የሚያዜሙበት፣ ዓባይ ቅኔ ነው ሊቃውንቱ የሚቀኙበት፣ ዓባይ መንገድ ነው ሕዝብ ሁሉ በስልጣኔ የተጓዘበት፣ ዓባይ ክብር ነው ታላቅነት የሚገለጥበት፣ ዓባይ ዝና ነው ኀያልነት የሚነገርበት፣ ዓባይ ቀለም ነው ውበት የሚገለጽበት፣ ዓባይ እስትንፋስ ነው የደረቀች ምድር የምትለመልምበት፣ የተጠማች ነብስ ጠጥታ የምትረካበት፡፡

ዓባይ እሴት ነው ትናንትና ዛሬ የተሳሰሩበት፣ ዓባይ ተስፋ ነው በዙሪያው ያሉ ሁሉ ነገን አሻግረው የሚያዩበት፣ ዓባይ ምግብ ነው የተራቡት የሚጠግቡበት፣ ዓባይ ድልድይ ነው ከዘመን ዘመን የሚሸጋገሩበት፣ ዓባይ መልክ ነው በዓለም ሁሉ የሚታወቁበት፤

የኢትዮጵያ እረኞች ተቀኝተውለታል፣ ሊቃውንቱ ዜማን ቀድተውበታል፣ ጥበብን ጨልፈውበታል፣ የግብጽ ፈርኦኖች እጅ ነስተውለታል፣ የደረቀችዋ ምድር አባት ሲሉ አክብረውታል፣ ከምንም ከማንም በላይ አስበልጠውታል፣ የግሪክ ባለቅኔዎች እና ፈላስፋዎች ጽፈውለታል፡፡ ዓባይ ከርዝመቱ ይልቅ ውበቱ እና ምስጢራዊነቱ እየጎላባቸው እጹብ ብለውታል፡፡

ኢትዮጵያ ዓባይን ለሌሎች ስትሰጥ ኖረች፣ ከዓባይ ጸጋም ሳትካፈል ዘመናትን አሳለፈች፡፡ ነገሥታቶቿ ከዓባይ ጸጋ ለመጠቀም አስበዋል፣ ሞክረዋልም፣ ዳሩ ዘመኑ ገና ነበርና ዘመን ይፍታው፣ የሚችል ትውልድም ይግጠመው ሲሉ የሀሳባቸውን ቋጠሮ ለትውልድ ሰጡት፡፡ እነሆ ከዚህ ዘመንም ደረሰ፡፡ የዘመናት የሃሳብ ቋጠሮ መፍቻ ለዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን ኾነ፡፡ ኢትዮጵያውያን ዓባይን ይጠቀሙበት ዘንድ በሀገሩ መሬት ማረፊያ አዘጋጁለት፡፡

ኢትዮጵያውያን ለወንዛቸው ማረፊያ እናዘጋጅለት ባሉ ጊዜ እሰየው፣ ደግ አድርጉ ያላቸው አልነበረም፡፡ የሚቃወማቸው እና ፈተና የሚደራርብባቸው በዛ እንጂ፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን የሚወርድባቸውን ውርጅብኝ ተቋቁመው ዓባይን እየገደቡት ነው፡፡

በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የብሉ ናይል የውኃ ምርምር ተቋም ተመራማሪ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር አበበ ይርጋ ኢትዮጵያ ግድቧን ወደ ማጠናቀቅ እየቀረበች መኾኗን ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በነበረባት የፖለቲካ ቀውስ፣ የደኅንነት ቀውስና ማኅበራዊ ችግር ውስጥ ኾና ግድቡን እዚህ ማድረሷ የሚደነቅ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም በርካታ ውኃ መያዝ እንደሚቀራት እና የግንባታ ሂደቱንም ማጠናቀቅ እንደሚጠበቅባት ነው የገለጹት፡፡ ዓባይ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ፣ ለጎረቤት ሀገራት በመሸጥ ገንዘብ እንደሚያስገኝና የሚኖርን ግንኙነት እንደሚያጠናክር ነው የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ የዲፕሎማሲ ትሩፋትን ታገኝበታለች፤ በሃብቷም ከፍ ትልበታለች ነው ያሉት፡፡ በኀይል እጥረት የሚሰቃየውን የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ፍቱን መድኃኒት ኾኖም ይመጣል ዓባይ፡፡ የዓባይ ግድብ አራተኛ ዙር የውኃ ሙሌት መሞላት የውኃ እጥረት ይገጥመናል፣ ሕዝባችን ይራባል በሚል ሲነሳ የነበረውን ሀሰተኛ ጩኸት ያጋለጠ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የዓባይ ግድብ የውኃ ሙሌት የግብጽን ሀሰተኛ ትርክት እና ፕሮፓጋንዳ ያመክናልም ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያ ውኃ ይዛ ግብጽ ምንም እንዳልኾነች እና አስዋን ግድብ ከወትሮው በተሻለ ውኃ ማግኘቱንም ተናግረዋል፡፡

የዓባይ ውኃ ሙሌት የግብጽን ሀሰተኛ ትርክት ለዓለም ያሳየ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን በፈተና እና በችግር ውስጥ ኾነውም ግድብ መገደብ እንደሚችሉ፣ ያሰቡትን ማሳካት እንደሚችሉ ያሳዩበት መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዓባይ ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በድርድር እና በውይይት የመፍታት ጽኑ አቋም እንዳላት የተናገሩት ተመራማሪው ድርድሯ ግን አሳሪ ስምምነቶችን የሚያመጡ መኾን እንደማይገባቸው ነው የተናገሩት፡፡ የዓባይ ጉዳይ ድርድር ቀጣይነት ያለው መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መሠረተ ልማት ሳያድግ፣ የመደራደሪያው ሜዳ ፍትሐዊ ሳይኾን፣ የውኃ መሠረተ ልማት ብዙ ሳይሠራበት ኢትዮጵያ በዓባይ ጉዳይ አሳሪ ስምምነት ማድረግ እንደማይገባትም ተናግረዋል፡፡ አሳሪ ስምምነቶች ራስን በራስ እንደማጥፋት እንደሚቆጠርም አንስተዋል፡፡ በግብጽ በኩል የሚነሳው የድርድር ሃሳብ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳና ኢትዮጵያ ወደፊት ልትገነባቸው የምታስባቸውን ግድቦች የሚከለክል መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ ኢትዮጵያ ዓባይን ከ98 በመቶ በላይ እንዳልተጠቀመችበት ያነሱት ተመራማሪው በምታፈልቀው ውኃ መጠቀምና ማደግ ይገባታል ብለዋል፡፡ አሳሪ ስምምነት መፈጸም ለዚህ ዘመን ትውልድ ብቻ ሳይኾን ለቀጣዩ ትውልድም እስርን ማስተላለፍ ይኾናል ነው ያሉት፡፡

የግድቡ ግንባታ ሂደት በተፋጠነ ቁጥር የኢትዮጵያ ተሰሚነት እየጨመረ፣ የመደራደር አቅሟ እየዳበረ፣ ጫናው እየቀነሰ፣ የታችኛው ሀገራት ሀሳብ እንዲቀየር እና ተሰሚነታቸው እየቀነሰ እንዲሄድ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡

ከተፋሰሱ ሀገራት እና ከምዕራባውያን ዘንድ የደረሰውን ጫና ተቋቁሞ ግንባታን ማሳለጥና ውኃ መሙላት ለኢትዮጵያ ታላቅ ነገር መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የዓባይ ጉዳይ ከአሁን በፊት ውኃ አትሙሉ የሚል እንደነበር ያነሱት ተመራማሪው አሁን ላይ አትሙሉ ሳይኾን ሙሊቱን አዘግዩልን ወደሚል መቀየሩንም ገልጸዋል፡፡ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በተለይም ግብጽ ከማስፈራራት ወደ ልመና መሸጋገሯን ተናግረዋል፡፡ የዓባይ ውኃ ሙሌት የግብጽን ፉከራ ያከሸፈ፣ የያዘችውን አቋም የሚያስቀይር እና ዲፕሎማሲያዊ ያልኾኑ አካሄዶቿን እንድትተው እንደሚያደርጋትም ገልጸዋል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሙሌት ለተፋሰሱ ሀገራት ምንም ጉዳት እንደማያስከትል የተረጋገጠ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ለተፋሰሱ ሀገራት የቤት ሥራ የሰጠ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ሲያደርሱ የነበሩ ሀገራት የግብጽን ሀሰተኛ መረጃ እየተረዱ እንዲሄዱ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያን እውነት ዓባይ ይናገራልም ነው ያሉት፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ትክክለኛውን መረጃ ለዓለም ማሳየትና ማስተዋወቅ እንደሚገባትም አመላክተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በምታመነጨው ወንዝ ማንም ነሺ ማንም ፈቃጅ ሊኾን አይችልምም ብለዋል፡፡

የዓባይ ግድብ የውኃ ሙሌት የኢትዮጵያ የተደራዳሪ ቡድን አባላቱ የሥነ ልቦና የበላይነት ይዘው እንዲቀመጡ እንደሚያደርጋቸውም ተናግረዋል፡፡ ለድርድር የሥነ ልቦና የበላይነት አስፈላጊ መኾኑን ያነሱት ተመራማሪው ሙሌቱ የታችኛው ሀገራት ከመደራደር ውጭ አማራጭ እንደሌላቸው እና ኢትዮጵያውያን በዓባይ ጉዳይ ወደኋላ እንደማይሉ ያሳየ ነውም ብለዋል፡፡ ዓባይ ሕዝብን ከረሃብና ከችግር የሚያላቅቅ መኾኑንም አንስተዋል፡፡

ግድቡ ላይ የሚሠራው ሥራ የድርድር አካሄዱን እየቀየረው እንደሚሄድም አመላክተዋል፡፡ የውኃ ሙሌቱ ግብጽ በዓባይ ላይ የሠራችውን ሀሰተኛ ሥራ ሁሉ ያሚያፈርስ እና እውነቱን ብቻ ለዓለም የሚያሳይ ነውም ብለዋል፡፡ ግብጽ ከዓባይ ውጭ አትኖርም፣ ዓባይም ከግብጽ ውጭ ለሌላ አይሰጥም የሚለውን ትርክት ፉርሽ አድርጎታልም ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ የ2016 ዓ.ም ትምህርት ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን አስታውቀ።
Next article“ ተስፋ መከራን ታሻግራለች፤ ክፉ ዘመንን ታሳልፋለች”