የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ የ2016 ዓ.ም ትምህርት ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን አስታውቀ።

72

ባሕርዳር፡ መስከረም 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ የ2016 ዓ.ም ትምህርት መስከረም 14 ቀን ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን አስታውቋል።

ትምህርት ሚኒስቴር በ5 ወረዳዎች ለመልሶ መቋቋም ያስገነባቸው ግንባታዎች እስከ መስከረም 30 ሥራ እንደሚጀምሩ የገለጹት የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ታደሰ ሸዋፈራ፤ በክልል ፈንድ በመንዝ ማማና ሸዋሮቢት ከተማ የተገነቡ ደረጃቸውን የጠበቁ 2 ትምህርት ቤቶችም ሥራ እንደሚጀምሩ ተናግረዋል፡፡

አቶ ታደሰ በክልሉ መንግሥት ከዚህ በፊት ተጀምረው የነበሩና በሞረትና ጅሩ ፣ በመንዝ ማማ እና አረርቲ ከተማ ግንባታቸው ተጠናቆ ተማሪዎች መቀበል መጀመራቸውን ተናግረዋል።

የትምህርተ ቤቶችን የውስጥ ግብዓት በማሟላት ረገድ ሰፊ ሥራ እየተሠራ ሲሆን 10 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የአይነት፣ የቁሳቁስና የጉልበት ተሳትፎ መደረጉንና ከዚህ ውስጥ 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ኃላፊው አንስተዋል፡፡

የሰው ኃይል ስምሪትን በተመለከተ አስቸጋሪ ሁኔታ መፈጠሩንና በተለይም የአመራር አገባብ የ1ኛ ደረጃ 93 በመቶ እና የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 90 በመቶ መሆኑን ገልጸዋል። በተመሳሳይ መምህራንም በዚሁ ልክ ወደ ሥራ እየገቡ እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡

የፀጥታ ችግር ባለባቸው የተለያዩ ወረዳዎች የተማሪዎች ምዝገባ መዋቅሩንና የአሠራር ሰንሰለቱን ጠብቆ ለመከወን ፈታኝ ሆኖብናል ፤ በዞኑ በአጠቃላይ በየደረጃው መመዝገብ ካለባቸው 685 ሺህ ተማሪዎች ውስጥ እስካሁን ድረስ 204 ሺህ ተማሪዎች እንደተመዘገቡና ይህም የእቅዱን 30 በመቶ እንደ ሆነ አቶ ታደሰ ግልጸዋል፡፡

በዞኑ በርካታ ተማሪዎች የሚመዘገቡባቸው ከነበሩት ወረዳዎች ውስጥ ሚዳ ፣ ግሼ ፣ መርሐቤቴ ፣ ሞረትና ጅሩ ፣ አሳግርት ፣ሀገረ ማርያም ፣ በረኸትና ምንጃር ጭራሽ ምዝገባ ያልተጀመረባቸው እና ምዝገባ ተጀምሮ የተቋረጠባቸው መሆኑን አንስተዋል። የግንኙነት አግባባችንም ፈጣንና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ጭምር አይደለም ብለዋል፡፡

አንፃራዊ ሰላም በሰፈነባቸው 15 ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ትምህርት ለማስጀመር የመጻሕፍ ስርጭት እና አይሲቲ ትምህርት በሚጀመርባቸው ትምህርት ቤቶች የመምህራን ቅጥር እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል፡፡

እንደ ዞን 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን መጻሕፍት የሚያስፈልጉ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው 877 ሺህ መጻሕፍት ክዘና ማዕከል መግባቱንና ከዚህ ውስጥ 244 ሺህ መጻሕፍት መሰራጨቱን ገልጸዋል፡፡

በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመጻሕፍት እጥረት ይገጥመናል ያሉት ኃላፊው መጻሕፍትን በሶፍት ኮፒ ከክልል በማምጣትና ለትምህርት ቤቶች በማድረስ ችግሩን ለማቃለል እየተሠራ መሆኑን ኃላፊው አመላክተዋል።

ኃላፊው አክለውም የትምህርት መሣሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ ለ2 ወረዳዎች 8 ሺህ ኮምፓይንድ ዴስክ ድጋፍ በማድረጉ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleተማሪዎች ለተሻለ ውጤት ከፍተኛ የሥነ ልቦና ዝግጅት ሰንቀው ወደ ትምህርት ገበታቸው ማቅናት እንዳለባቸው ተገለጸ።
Next article“ዓባይ የኢትዮጵያን እውነት ገልጧል”