
ባሕር ዳር: መስከረም 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ክረምቱ አልፎ መስከረም ሲጠባ ተማሪዎች የእረፍት ጊዜያቸውን አጠናቅቀው ወደ ትምህርት ገበታቸው የሚመለሱበት ወቅት በመኾኑ በጉጉት ይጠበቃል፡፡
ልጆች ከትምህርት ቤት፣ ከንባብ፣ ከመምህራን ርቀው የቆዩ በመኾናቸው ለአዲሱ የትምህርት ዓመት ከፍተኛ የሥነ ልቦና ዝግጅት ያስፈልጋቸዋል፡፡
የሥነልቦና ባለሙያው አቶ የሻምባው ወርቄ እንደሚሉት ተማሪዎች ለረጅም ጊዜ ከትምህርት ገበታቸው ተለይተው በመቆየታቸው ወደ ትምህርት ቤት ሲያቀኑ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ዝግጅት ማድረግ አለባቸው። ከፍተኛ የኾነ የትምህርት ተነሳሽነት ሊኖር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
አቶ የሻምባው ተማሪዎች ነገሮች አእምሮአቸው ላይ ለረጅም ጊዜ የሚያቆዩት በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴያቸው ደጋግመው ሲተገብሯቸው መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡
ተማሪዎች ለመማር ጉጉት ማሳየት፣ የተነሳሽነት ሥሜት መፍጠር፣ አካላቸው ብቻ ሳይኾን ልቦናቸውም ጭምር ወደ ትምህርት ቤት መሄድ አለበት ብለዋል፡፡
ተማሪዎች ጓደኞቻቸው እና ትምህርት ቤቱ ስለናፈቃቸው ብቻ ሳይኾን ፈልገውት፣ ወደውት፣ ራዕይ ሰንቀው መሄድ አለባቸው ነው ያሉት ባለሙያው። ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ የጠነከረ ዓላማ ሊኖራቸው እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ተማሪዎች መዳረሻቸውን ዐውቀውት መጓዝ ካልጀመሩ ውጤት አልባ የመኾን እድላቸው ከፍተኛ በመኾኑ ቀድመው ማለም ይጠበቅባቸዋል፡፡
ቀደም ሲል የነበራቸውን የትምህርት አፈጻጸም መገምገም፣ በቀጣይ ምን ብሠራ ነው ውጤታማ መኾን የምችለው የሚለውን ጥያቄም ራሳቸውን መጠየቅ እና ለጉዳዩ ኃላፊነትን መውሰድ አለባቸው ብለዋል የሥነ ልቦና ባለሙያው፡፡
አቶ የሻምባው ተማሪዎች የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልዶች በመኾናቸው በችግር ውስጥ ማለፍን፣ ጽናትን፣ እና በጎ ነገሮችን የመፍጠር ልምድን ማዳበር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ ትምህርት ከመጀመሩ በፊት ቀድመው መዘጋጀት እና ከፍ ያለ ሥነ ልቦና መገንባት ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል፡፡
የልጆችን ሥነ ልቦና በመገንባት በኩል የወላጆች ድርሻ ከፍ ያለ መኾን እንደሚገባውም ጠቁመዋል። “ልጆች ከተክሎች ጋር ይመሳሰላሉ” የሚሉት አቶ የሻምባው በልጅነታቸው መንከባከብ እና መዳረሻቸውን ማሳየት የወላጆች ድርሻ እንደኾነ መክረዋል፡፡
ወላጆች ለልጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁስ ገዝቶ ትምህርት ቤት መላክ ብቻ ሳይኾን አቅማቸውን መገምገም ፣ ጓደኞቻቻው ማጥናት ፣ ሥነ ምግባራቸውን በየጊዜው መገምገም አለባቸው ነው ያሉት። ጥሩውን ልምድ እንዲያሳድጉት መጥፎውን ደግሞ እንዲያስወግዱት ቁጥጥር ማድረግም ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
የወላጆች ክትትል እና ቁጥጥሩ ልጆች ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ብቻ እንዲያወዳደሩ እና ወደተሻለው መንገድ እንዲሄዱ ለማድረግ ብቻ መኾን እንዳለበትም መክረዋል፡፡
ወላጆች የትምህርት ዘመኑ ሲጠናቀቅ ለምን ከደረጃህ ወረድክ ማለት ብቻ ሳይኾን በኹሉም እንቅስቃሴ ላይ አብረው ተሰልፈው ከችግር ማሻገር እንጂ ከጠፋ በኋላ መፈለግ አግባብነት አለመኾኑን ጠቁመዋል፡፡
“ልጆች በልጅነት ዘመናቸው ጫና ቢደርስባቸው ከዚህ ጫና የማውጣት ኀላፊነት የወላጆች ነው” የሚሉት ባለሙያው ወላጆች የሚያዩዋቸውን ነገሮች ለልጆች ከማጋራት መቆጠብ እንዳለባቸው መክረዋል፡፡
አኹን ያለው የሰላም ኹኔታ በልጆች የወደፊት ራዕይ ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ወላጆች በልጆቻቸው ፊት የሚያወሩትን ርእሰ ጉዳይ መምረጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ተማሪዎች ነጋቸውን በራዕይ ሰንቀው የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲገኙ ወላጆች ምቹ ኹኔታ መፍጠር እንዳለባቸውም መክረዋል፡፡ ልጆች በሚያዩት አልባሌ ነገር ተስበው ከትምህርት ገበታቸው መስተጓጎል እንደሌለባቸውም አቶ የሻምባው አስረድተዋል፡፡
የመማሪያ ቁሳቁስ አለመሟላት፣ የተማሪዎች የደንብ ልብስ አለመኖር እና ሌሎች ችግሮች ተማሪዎችን እደርስበታለሁ ብለው ካሰቡት እንዳይደርሱ እንቅፋት ሊኾኑ አይችልም፤ ይልቁንስ በችግር ውስጥ አልፎ ለትልቅ ደረጃ ለመድረስ ማለምን ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ “የአሁኑ ሂደት የወደፊት ማንነትን እና ደረጃን ይወስናል” የሚሉት ባለሙያው ተማሪዎች ራሳቸውን መኾን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
ወላጆች ደብተር መግዛት ባይችሉ ተማሪዎች ችግሩን መጋፈጥ እና ነገ የሚደርሱበትን ደረጃ ላለማጣት ከፍ ያለ ሞራል መገንባት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!