
ባሕርዳር፡ መስከረም 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊነት የተሞላበት የስደተኞች አያያዝ የሚደነቅ ነው ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዲ ገለጹ።
78ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ በኒው ዮርክ እየተካሄደ ነው። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ ነው።
ከጉባኤው ጎን ለጎን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዲ ጋር ተወያይተዋል።
ፍሊፖ ግራንዲ ኢትዮጵያ በስደተኞች ላይ ያላት ፖሊሲና የሱዳን ስደተኞችን ሰብዓዊነት በተሞላበት መልኩ ተቀብላ እያስተናገደች ያለችበትን መንገድ አድንቀዋል።
ለጋሽ አካላት በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩም ጥሪ አቅርበዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከ78ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን ከተለያዩ አገራት ልዑካን ጋር የጋራ ፍላጎት በሆኑ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ስኬታማ ውይይቶችን ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!