
ባሕር ዳር: መስከረም 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ተማሪዎች ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ለትምህርታቸው ብቻ ትኩረት ሰጥተው ውጤታማ ለመኾን እየተዘጋጁ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ተማሪዎቹ የትምህርት ዘመኑን በውጤታማነት ለማጠናቀቅ ከክረምት ጀምረው አስፈላጊውን ዝግጅት ሲያካሂዱ መቆየታቸውን አንስተዋል። አሁንም የሚያስፈልጉትን ግብዓቶች አሟልተው የትምህርት መጀመርን ብቻ እንደሚጠባበቁ ነው ያስገነዘቡት፡፡
ተማሪ ያበጀ ጀጃው እንደሚለው ትምህርት ቤታቸው ለትምህርት በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት በዝጉም ወቅት ቤተ መጽሐፍት ክፍት ኾኖ አስፈላጊውን አገልግሎት ሲሰጣቸው መቆየቱን ነግሮናል፡፡ ሁሉም ተማሪዎች የተመቻቸላቸውን እድል ተጠቅመው አስፈላጊውን ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ገልጿል።
ካደረጉት ዝግጅት አንጻር ሲታይም የትምህርት ዓመቱን በውጤታማነት እንደሚያጠናቅቁ ነው የተናገረው፡፡ ተማሪዎች ለውጤት እንዲበቁ መምህራን አስፈላጊውን እገዛ ሲያደርጉ እንደቆዩም ገልጿል፡።
ተማሪ አሮን ፈቃዱ የትምህርት ባለድርሻ አካላት በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የትምህርት ጥራት እንዲመጣ አስፈላጊውን እገዛ ማድረጋቸውን ነግሮናል፡፡
ከወላጆቻቸው እገዛ ባለፈ መምህራን እና የትምህርት አመራሩ እያደረገ ያለው እገዛ የተሻለ ውጤት እንዲመጣ እንደሚያግዝ ገልጿል፡፡
መምህራን ተማሪዎች አቅማቸው እየተለየ እገዛ እየተደረገላቸው እንደኾነ ጠቅሰዋል። በቀጣይም ተማሪዎች ውጤታማ እንዲኾኑ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርጉም ነው የገለጹት፡፡
በተለይም ተማሪዎች በአጋዥ መጽሐፍት ታግዘው ለትምህርት ዘመኑ ብቁ የኾነ እውቀት እንዲያገኙ ለማስቻል እገዛቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!