
ባሕር ዳር: መስከረም 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማርክ ሱዝማን ጋር በኒው ዮርክ ተወያይተዋል። በውይይቱ ኢትዮጵያ እና ፋውንዴሽኑ ያላቸውን ትብብር አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ ሰላምን ለማጽናት እየሠራች እንደምትገኝና የ10 ዓመት የልማት እቅድ እየተገበረች መኾኑን ጠቅሰው ለዚህም አጋር አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ ጠንካራ የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ መቀጠሏንና እንደ ሀገር ፈተናዎችን መቋቋም የሚችል ጠንካራ አቅም መገንባቷን አመልክተዋል።
የስንዴ ምርት እና የሌማት ትሩፋት በሀገር ደረጃ ስኬት የተገኘባቸው ፕሮጀክቶች መኾናቸውንም ገልጸዋል።
ከልማት አጋሮች ጋር ያለውን ትብብር አበረታች መኾኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የጀመራቻቸውን መልካም ትስስር የመፍጠር ሥራዎች አጠናክራ እንደምትቀጥል አመልክተዋል።
ማርክ ሱዝማን በበኩላቸው ፋውንዴሽኑ ከኢትዮጵያ ጋር በጤና፣ ግብርና፣ ዲጂታል ፋይናንስና ሌሎች መስኮች ጠንካራ ትብብር እንዳለው አንስተዋል።
ፋውንዴሽኑ ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራት ቁርጠኛ መኾኑንና ከኢትዮጵያ የልማት መርሐ-ግብሮች ጋር በተጣጣመ መልኩ ያለውን ትብብር ይበልጥ እንደሚያጠናክር መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!