
ባሕር ዳር: መስከረም 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል የትምህርት ሳምንት እየተከበረ ነው፡፡ በትምህርት ሳምንቱ የዓመቱ መደበኛ ትምህርት ከመጀመሩ አስቀድሞ ሊደረጉ የሚገባቸው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ተብሏል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኅላፊ እየሩስ መንግሥቱ የትምህርት ሳምንት በአማራ ክልል በትምህርት ቤቶች እየተከበረ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የትምህርት ሳምንት ሲከበር አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት ማስተዋወቅ ቀዳሚው ተግባር መሆኑን አንስተዋል፡፡ ባለፈው የትምህርት ዘመን በክላስተር ደረጃ ለመምህራን ሥልጠና መስጠቱን ያወሱት ምክትል ቢሮ ኅላፊዋ የሠለጠኑት መምህራን ቁጥር አነስተኛ ነበር ብለዋል፡፡
የሠለጠኑ ውስን መምህራን ያልሠለጠኑ መምህራንን በትምህርት ቤት ደረጃ በትምህርት ሳምንት ማሠልጠን እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል፡፡ በትምህርት ሳምንቱ የአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ትውውቅ እየተደረገ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ የ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የእቅድ ትውውቅ እና የእቅድ ዝግጅት ክለሳ ጊዜ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ትምህርት ቤቶቹን ለመማር ማስተማሩ ሥራ ምቹ ማድረግ በትምህርት ሳምንቱ ከሚተገበሩ ጉዳዮች መካከል መኾኑም ተመላክቷል፡፡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ሲመጡ ትምህርት ቤቱ ማራኪ ኾኖ እንዲጠብቃቸው እየተሠራ ነውም ብለዋል፡፡ በአማራ ክልል የተማሪዎች ምዝገባ መራዘሙን የገለጹት ምክትል ቢሮ ኅላፊዋ በትምህርት ሳምንቱ የተማሪዎች ምዝገባ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡
የዓመቱ የትምህርት ሥራዎች ውጤት የሚመዘነው አስቀድመው በተሠሩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ልክ መኾኑን ያነሱት ወዘይሮ እየሩስ በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ጥሩ ጥሩ ሥራዎች ከተሠሩ የምንፈልገውን ውጤት ማስመዝገብ እንችላለን ነው ያሉት፡፡ በትምህርት ሳምንቱ በዓመቱ የትምህርት ሥራዎች ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ የሚደረስበት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
“በትምህርት ሳምንት ወቅት የሚከናወኑ ተግባራት በዓመቱ ለሚመዘገበው ስኬት ትልቅ ድርሻ አላቸው” ያሉት ምክትል ቢሮ ኅላፊዋ ባለፉት ዓመታት የታዩ ክፍተቶችን በመሙላት መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
ምክትል ቢሮ ኅላፊዋ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል እና የትምህርት ሥርዓቱን ለማዘመን ከመንግሥት ባለፈ ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!